በአፋር ክልል እርዳታ ጭኖ ሲጓዝ በነበረ ተሽከርካሪ ውስጥ በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ተያዘ

158

ሐምሌ 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) እርዳታ ጭኖ ሲጓዝ በነበረ ተሽከርካሪ ውስጥ በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ መያዙን በአፋር ክልል የጉምሩክ ኮሚሽን የሰመራ ቅርጫፍ ሰርዶ መቆጣጠሪያ ጣቢያ አስታወቀ።

የጣቢያዉ አስተባባሪ ኮማንደር አህመድ ሳልህ እንደገለጹት፤ በፍተሻ ጣቢያዉ በህገወጥ መንገድ የሚዘዋወሩ ነዳጅና ጥሬ ገንዘብን ጨምሮ የተለያዩ ቁሳቁሶች እየተያዙ ነው።

ባለፈዉ ሳምንትም በጣቢያዉ በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ ከ8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ጥሬ ገንዘብ መያዙን አስታውሰው፤ ዛሬ ጠዋት 3 ሰአት ላይ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ3-A10298 የተሳቢ ሰሌዳ ቁጥር 23634 በሆነ ከባድ ተሽከርካሪ ውስጥ 2 ሚሊዮን 280 ሺህ 640 ብር ሊያዝ መቻሉን ተናግረዋል።

ተሽከርካሪው የእርዳት እህል ጭኖ ሲጓዝ እንደነበረም አመልክተዋል።

ከገንዘቡ በተጨማሪ የወርቅ ሚዛንና ሌሎች ቁሳቁሶችም በተሽከርካሪው ውስጥ በጣቢያው የፍተሻ ሰራተኞች መያዙን ገልጸዋል።

መኪናዉና አሽከርካሪዉ በህግ ቁጥጥር ስር ዉለዉ ተጨማሪ ምርመራ እየተደረገባቸዉ እንደሚገኘም የጣቢያ አስተባባሪዉ ኮማንደር አህመድ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም