የሲዳማ ክልል ለሙስና ተጋላጭ የሆኑ አሰራሮችና ክፍተቶችን ለመድፈን ጠንከር ያለ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ

304

ሀዋሳ፣ ሐምሌ 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) የሲዳማ ክልል ለሙስና ተጋላጭ የሆኑ አሰራሮችና ክፍተቶችን ለመድፈን ክትትል እንደሚያደርግና ጠንከር ያለ እርምጃ እንደሚወስድ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።

በክልሉ ፈጣን ልማትና በአገልግሎት አሰጣጥ የህብረተሰብ እርካታ ለማረጋገጥ በየደረጃው የሚገኘው አመራር በቁርጠኝነት እንዲሰራ የክልሉ ርእሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ አሳሰቡ።

ለስድስት ቀናት በሀዋሳ ከተማ የተዘጋጀው የክልሉ የ2014 በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀም ግምገማና የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ ፈፃሚ ማዘጋጃ መድረክ ዛሬ ማምሻውን ተጠናቋል።

በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ ርዕሰ መስተዳድሩ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ፈጻሚውና አመራሩ የተሰጠውን ተልዕኮ የተወጣበት መንገድ በጥልቀት ተገምግሟል።

መድረኩ አመራሩ በቀጣይ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የሚያስችለው ብቁ ቁመና የታጠቀበት ነው ብለዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋና ወጪ ቆጣቢ እንዲሆን በማድረግ በኩል ክፍተት እንደነበር ገልጸው፤ በተያዘው በጀት ዓመት ጉድለቶቹ የሚታረሙበት ዕቅድ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ ዕቅድ መዘጋጀቱን ገልጸው፤ አመራሩ ዕቅዱን በቁርጠኝነት እንዲያስፈጽም መግባባት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል።

ለሙስና ተጋላጭ የነበሩ አሰራሮችና ክፍተቶችን ለመድፈን በተወሰደ እርምጃ ውጤት ቢመጣም አመራሩ ያልተገባና የተጋነነ ውሎ አበል የመውሰድ አዝማሚያ ውስጥ እየገባ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

በዚህ ላይ የክልሉ መንግሥት ጠንከር ያለ ክትትል እንደሚያደርግና እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል በበልግ ዝናብ እጥረት የተስተጓጎለውን የግብርና ልማት በተያዘው መኸር እርሻና በቀጣይ የበጋ መስኖ ለማካካስ እንዲቻል በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ በበኩላቸው መድረኩ በጥንካሬዎችን ለማስቀጠል እና በተግባር ሂደት የታዩ ድክመቶችን ለማረም ገንቢ ሚና ተጫውቷል ብለዋል።

በ2015 ዋና ዋና ግቦች ላይ አመራሩ ግልፀኝነትና የጋራ አቋም በመያዝ የመንግስት እና የፓርቲ ስራዎችን በውጤታማነት መፈፀም እንዲቻል መድረኩ አቅም መፍጠሩን ገልጸዋል።

አመራሩ የህዝቦችን አብሮነትንና አንድነትን የሚያጎለብቱ፣ የዜጎችን የኢኮኖሚ፣ የመልካም አስተዳደርና የዴምክራሲ ፍላጎቶች ምላሽ ለመስጠት መረባረብ እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።

ሁለንተናዊ ብልጽግናን የማረጋገጡን ግብ ለማሳካት መሰረት እየጣለን መሄድ ይገባናል በማለት ገልጸው፤ ውስን የሆነውን ሀብት በአበልና በስልጠና ማባከን ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

በዚህ ዓመት በሀዋሳ ዙሪያና ሎኮ አባያ ወረዳዎች የተጀመረውን የበጋ መስኖ ወደ ሌሎች አካባቢዎች በማስፋፋት ለማልማት አቅጣጫ መያዙን አስታውቀዋል።

በተጠናቀቀው በጀት አመት ብልሹ አሰራሮችንና ሙስናን ለመከላከል በተደረገው እንቅስቃሴም 248 አመራሮች ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ሲደረግ 140 አመራሮች ደግሞ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው አብራርተዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ አመራሮች የእውቅና ሠርተፊኬት፣ ዋንጫና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።