በኢትዮጵያ የመረጃ ነጻነትና ግለኝነትን ባማከለ አግባብ የበይነ መረብ አስተዳደር ሥርዓት መዘርጋትና መልክ ማስያዝ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

266

ሐምሌ 28 ቀን 2014(ኢዜአ) በኢትዮጵያ በየዕለቱ መልኩን እየለዋወጠ የሚገኘውን የበይነ መረብ የመረጃ ነጻነት፣ ግለኝነትና አካታችነትን ባማከለ አግባብ የበይነ መረብ አስተዳደር ሥርዓት መዘርጋትና መልክ ማስያዝ እንደሚገባ ተገለጸ።

የመጀመሪያውን ብሔራዊ መረብ አስተዳደር ጉባኤ "በይነ መረብ ለአካታች ልማት” በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።


በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አዘጋጅነት በተካሄደው በዚህ ጉባዔ የፌደራልና የክልል የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች፣ የግሉ ዘርፍ፣ ሲቪል ማኀበራትና ሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች ተገኝተዋል።


የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ በአራተኛው ኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን የሰዎች ዕለታዊ ክዋኔዎች በበይነ መረብና መሰል የግንኙነት አውታሮች ተጽዕኖ ሥር ወድቀዋል ብለዋል።


በይነ መረብና መሰል የግንኙነት አውታሮች በጥልቀትና በስፋት በየዕለቱ የሚለዋወጡና በሰዎችና ተቋማት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መሰረታዊ ለውጦች እያመጡ መሆኑንም ተናግረዋል።


በየቀኑ እያሻቀበ በሚገኘው የበይነ መረብ ተጠቃሚዎች አሃዝ የፈጠራ አቅምና የሀሳብ ልውውጥ በማሳለጥ ለሁለንተናዊ ዕድገት አዎንታዊ ሚና ቢኖረውም አሉታዊ መልኮችም እንዳሉት ጠቅሰዋል።


በይነ መረብ ሁሉንም የሚመለከትና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ የበይነ መረብ አገልግሎት አካታች፣ ተደራሽ እና የሕዝብ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ አግባብ መመራት እንዳለበት ተናግረዋል።


ዲጂታል አትዮጵያን ዕውን ለማድረግ ቴክኖሎጂን የሚረዳና የሚጠቀም በዲጂታል ማኅበረሰብ ግንባታ ላይ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ተቋማዊና አገራዊ ጥረቶችም ከዓለም አቀፍ ሥራዎች ጋር ማስተሳሰር ላይም ተተኩሯል ነው ያሉት።


በይነ መረብ በአግባቡ ካልተመራ ሳይበር ጥቃትና የተዛባ መረጃ ሥርጭትና መሰል ፈተናዎች እንዳሉ ገልጸው፤ እንደ አገር ስጋቶችን ለመቀልበስ በኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ የሕግ ማዕቀፍ ያስፈልጋል ብለዋል።


በዚህም የበይነ መረብ ግንኙነት ለመሳለጥና የሕዝብ አስተማማኝ ደኅንነት የተጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት የኮምፒዩተር ወንጀል አዋጅ ሥራ ላይ የዋለ ሲሆን የግል መረጃ ጥበቃ አዋጅ ረቂቁ ተዘጋጅቷል ብለዋል።


በዝግጅት ላይ የሚገኙና የተዘጋጁት ፖሊሲና ስትራቴጂዎችም ከዓለም አቀፍ የበይነ መረብ ሕግጋት ጋር የተጣጣሙና ከአገር በቀል ኢኮኖሚና የአሥር ዓመት መሪ ዕቅድ ጋር የተናበቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።


ኢትዮጵያ ከወራት በኋላ የምታስተናግደው የዓለም አቀፉ የበይነ መረብ ጉባዔ የበይነ መረብ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅሞች፣ ተመጣጣኝና አቅም ያለው የበይነ መረብ ተደራሽነትና መብቶች ላይ ያጠነጠነ መሆኑን አመላክተዋል።


የበይነ መረብ አስተዳደር ሥርዓት መዘርጋት እንደሚያሻም ገልጸዋል።


የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ባልቻ ሬባ የዛሬዋ ዓለም ሚሊዮኖች ዕለታዊ ሥራዎችን በበይነ መረብ እንደሚከውኑና ዲጂታል ሽግግር ለተለዋዋጩ ዓለም ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።


የተዛባ መረጃ ሥርጭት በርካቶችን ለመገለል እና የወጣቶችን አዕምሮ ለመበረዝ እንደሚዳርጉ ገልጸው፤ በዚህም ጥቅሞችን በማጎልበትና ስጋቶችን በመቀነስ በበይነ መረብ መልክ ማስያዝ የአገራት ዐቢይ ትኩረት ነው ብለዋል።


ግጭት ቀስቃሽ ጉዳዮችን መቆጣጠር ሁሉም ለሚናፍቅ የነገ የጋራ ዓለም ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚያስፈልግ፣ ለዚህም የወደፊት የበይነ መረብ ዕጣ-ፈንታ መልክ ማስያዝ በጋራ መሥራት ይጠይቃል ነው ያሉት።


ለአገር አስፈላጊ የሆነውን በይነ መረብ የመረጃ ነጻነትና ግለኝነትን ባማከለ አስተዳደር ሥርዓት ለመዘርጋት መንግሥትና የኢንዱስትሪው ተዋናዮች ሃሳብ ማመንጨት እንደሚጠይቅም አንስተዋል።


የኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን ከተቋቋመ ሦስት ዓመታት ሲሆን አስፈላጊ የክትትልና ቁጥጥር የሕግ ማዕቀፎችን ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።


የኢትዮ-ቴሌኮም ቺፍ ኢንፎርሜሽን ሴኪዩሪቲ ኦፊሰር አቶ ፀጋዬ አማኑኤል ተቋሙ ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስኬት ትልቁን ሚና እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።


ተቋሙ በቅርቡ ያስጀመረውን አምሰት ትውልድ በይነ መረብ አገልግሎት (ፎርጂ) ማቅረብን ጨምሮ ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም የሞባይል በይነ መርብ ተጠቃሚዎች 25 ሚሊየን ማድረሱን፤ በዋጋ ተመጣጣኝነት 43 በመቶ መቀነሱን፣ በተደራሽነት 99 ነጥብ 1 በመቶ ሲያሳድግ፣ በመልካዓ ምድራዊ ሽፋን 88 ነጥብ 5 በመቶ ማደጉን ገልጸዋል።


የኢትዮጵያ ስራ ፈጣሪ ማኅበር ፕሬዚዳንት እና የበይነ መረብን ጉባዔ አማካሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሳሚያ አብዱልቃድር ጉባዔው ከበይነ መረብ ጋር ተያይዞ ያሉ ዕድሎችና ፈተናዎችን የተመለከቱ ለፖሊሲ አውጪዎች የሀሳብ ግብዓት እንደሚጠቅም ገልጸዋል።


ኢትዮጵያ በቀጣይ ዓመት ወርኃ ህዳር ለማስተናገድ ለተመረጠችበት 17ኛው ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ በስኬት እንዲካሄድ መሰረት እንደሚጥልም ይጠበቃል።


በአውሮፓዊያኑ 1983 ዓ.ም በአሜሪካ የተጀመረ በይነ መረብ በኢትዮጵያ ደግሞ ከ14 ዓመታት በኋላ በ1997 ዓ.ም የጀመረ የኔትወርክ አውታር ነው።


በ2006 ዓ.ም በአቴንስ የመጀመሪያ ጉባዔ ከተካሄደ በኋላ በየዓመቱ እየተካሄደ ሲሆን ዘንድሮ ለሚካሄደው 17ኛው ጉባዔ ከህዳር 19 እስከ 20 በአዲስ አበባ ከተማ ይካሄዳል።


ከ192 አገራት የተውጣጡ ከ2 ሺህ በላይ ተሳታፈዎች በአካልና በበይነ መረብ በሚታደሙበት ዓለም አቀፍ በይነ መረብ አስተዳደር ጉባዔ ለኢትዮጵያ መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም