የሐረሪ ክልል ምክር ቤት ለ2015 በጀት ዓመት ከ3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት አጸደቀ

164

ሐምሌ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) የሐረሪ ክልል ምክር ቤት ስድስተኛ ዙር፣ አንደኛ ዓመት ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ለ2015 በጀት ዓመት 3 ቢሊየን 450 ሚሊየን ብር በጀት አጽድቋል።

በክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ የቀረበው በጀት 1 ቢሊዮን 361 ሚሊዮን ብር ከክልሉ ገቢ የሚሰበሰብ ሲሆን ቀሪው ከፌደራል መንግስት ድጎማ እንደሚገኝ ተገልጿል።

በተያያዘ ዜና ምክር ቤቱ ለ10 ዓመት የሚያገለግል አዲስ የሐረር ከተማ መዋቅራዊ ፕላን አጽድቋል።

የሐረሪ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ አዩበ አህመድ መዋቅራዊ ፕላኑን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የቀድሞ የከተማው መዋቅራዊ ፕላን የአገልግሎት ጊዜ በማብቃቱ አዲስ ፕላን ማስፈለጉን ገልጸዋል።

መዋቅራዊ ፕላኑ በክልሉ በከተማ እና ገጠር ፍትሀዊ ልማት እንዲኖር ለማስቻል እና ከተማና ገጠሩን በማስተሳሰር የመሰረተ ልማቶችን ለሟሟላት ከፍተኛ የሆነ ፋይዳ ያለው መሆኑን የሐረሪ ክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ተናግረዋል።

በአሁኑ ጊዜ አርሶ አደሩ በደላሎች ከእርሻው ላይ መሬቱን እየሸጠ እየተፈናቀለ ለችግር እየተዳረገ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ፕላኑ አርሶ አደሩ ከእርሻው እንዳይፈናቀልና ባለበት ቦታ ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ እንደሚያመቻች አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም