ሁለት ሰዎችን በመግደል በውኃ መፍሰሻ ቱቦ ውስጥ የጨመሩት የጥበቃ ሠራተኞች በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ተቀጡ

106

ሐምሌ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ)በአምስት ቀናት ልዩነት ውስጥ ሁለት ግለሰቦችን ነፍስ በማጥፋት አስክሬናቸውን በውኃ መፍሰሻ የመንገድ ቱቦ ውስጥ የከተቱት የጥበቃ ሠራተኞች በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ተቀጡ።

በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያሳየው 1ኛ ተከሳሽ ዘካሪያስ ኮዶ 2ኛ ተከሳሽ ዮሐንስ ማጠሉ 3ኛ ተከሳሽ አስራት አበበ የተባሉት ተከሳሾች በተለያየ ጊዜ በመገናኘት ባጃጅ ከግለሰቦች ላይ በኃይል ለመንጠቅ ሲመካከሩ እና ሲዘጋጁ ቆይተው ጥር 27 ቀን 2013 ዓ.ም ከምሽቱ 02:30 ሲሆን በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ክልል ልዩ ቦታው ቦሌ ቡልቡላ ሙሉ ወንጌል አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የባጃጅ ባለቤት የሆነው ሟች ማናየ እንየውን በ30 ብር ኮንትራት በማናገር ወደ ሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን እንዲወስዳቸው በመስማማት አድርሷቸው ከባጃጁ ሊያወርዳቸው ሲቆም 3ኛ ተከሳሽ ሟችን በክርኑ አንቆ ሲይዘው 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች የሟችን እግር በጋራ ይዘው በማውረድ መሞቱን ሲያረጋግጡ ከቤተ ክርስቲያኑ ፊት ለፊት ካለ የመንገድ ቱቦ (የውኃ መውረጃ) በመክተት የሟችን 500 ብር የሚገመት ስልክ እና 185 ሺህ ብር የሚገመት ባጃጅ ወስደዋል።

በተጨማሪም የካቲት 2 ቀን 2013 ዓ.ም ከምሽቱ 03:30 ሰዓት ሲሆን 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች የመጀመሪያውን ወንጀል ከፈጸሙ ከአምስት ቀን በኋላ ምትኩ መለሰ የተባለን ግለሰብ 1ኛ ተከሳሽ የጀኔሬተር ባትሪ ሊሸጥለት በተስማሙት መሠረት ደውሎ እንዲመጣ በማድረግ ተከሻሶች በጥበቃ ሠራተኝነት ተቀጥረው ከሚሰሩበት ሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን ጊቢ ውስጥ እንዲገባ እና እንዲደበቅ ካደረገው በኋላ 2ኛ ተከሳሽ “ሌባ ሌባ” በማለት ሟችን በያዘው የጥበቃ ዱላ ጭንቅላቱን ሲመታው 1ኛ ተከሳሽም ሟች በወደቀበት የመታው በመሆኑ ሕይወቱ ሲያልፍ 450 ብር የሚገመት ስልኩን እና ይዞት የነበረውን 3 ሺህ ብር በመውሰድ ከአሁን በፊት የማናየ እንየውን አስክሬን በከተቱበት ቱቦ ውስጥ በመደበቃቸው ተከሳሾች በፖሊስ ክትትል እና በኅብረተሰቡ ድጋፍ ተይዘው በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዲሪ የወንጀል ሕግ በመተላለፍ በፈጸሙት የሰው መግደል እና ከባድ የውንብድና ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸውዋል።

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሰው መግደል ወንጀል ችሎት የቀረቡት ተከሳሾች ድርጊቱን አልፈፀምንም በሚል የእምነት ክህደት ቃላቸውን የሰጡ በመሆኑ ዐቃቤ ሕግ ያሰባሰባቸውን የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎች በማቅረብ ተከራክሯል።

ተከሳሾችም መከላከያ ማስረጃ በማቅረብ ያሰሙ ቢሆንም በዐቃቤ ሕግ የቀረበውን የሰው እና የሰነድ ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻላቸው ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹን በተከሰሱበት አንቀፅ ስር ጥፋተኛ ናቸው ብሏል።

በመጨረሻም ሐምሌ 25 ቀን 2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች የፈፀሙት ተደራራቢ ወንጀል በመሆኑ በሁለቱም ክሶች አንድ የቅጣት ማክበጃ በመያዝ እያንዳንዳቸው በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጡ 3ኛ ተከሳሽ 4 የቅጣት ማቅለያ ተይዞለት በ15 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን ከፍትሕ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም