ፓኪስታን በሰነድ አያያዝ ፣የመረጃ ደህንነት እና መረጃ አስተዳደር ዙሪያ የቴክኖሎጂ ሽግግር ታደርጋለች

161

ሐምሌ 26 ቀን 2014 (ኢዜአ)ፓኪስታን በሰነድ አያያዝ ፣የመረጃ ደህንነት እና መረጃ አስተዳደር ዙሪያ ለኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ገለጸች።

በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር ከፓኪስታን የብሔራዊ መረጃ እና ምዝገባ ባለሥልጣን ዳይሬክተር ሙሐመድ ታሪቅ ማሊክ ጋር ውይይት አድርገዋል።

በውይይታቸው የፓኪስታን የብሔራዊ መረጃ እና ምዝገባ ባለሥልጣን ለኢትዮጵያ በሰነድ አያያዝ፣የመረጃ ደህንነት እና መረጃ አስተዳደር ዙሪያ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

በዘርፉ ቀልጣፋና አስተማማኝ የአገልግሎት አሰጣጥ፣የወሳኝ ኩነት ምዝገባና አስተዳደር፣የዜጎች ብሄራዊ ዲጅታል መታወቂያ ምዝገባና አደረጃጀትና ዘመናዊ የአሰራር ስርዓት ተሞክሮ እና ቴክኖሎጂ ማሸጋገር በሚቻልበት ሁኔታ ሰፊ ውይይት ማካሄዳቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

አምባሳደር ጀማል በከር በፓኪስታን የተከፈተው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከለያቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህ ረገድ የፓኪስታን የዳበረ ልምድና ተሞክሮ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ተግባራዊ ድጋፍ በማድረግ ዙሪያም ተወያይተዋል፡፡

ይህ የቴክኖሎጂ ሽግግር ትብብር ኢትዮጵያ የተያያዘችውን ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግር የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።

የፓኪስታን የብሔራዊ መረጃ እና ምዝገባ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሙሐመድ ታሪቅ ማሊክ በበኩላቸው ኢትዮጵያን በቅርበት የሚያውቁና ባለሥልጣኑ ያለውን እውቀት፣ቴክኖሎጂና ክህሎት ለሽግግርና ድጋፍ ለማድረግ መንግስታቸው ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም