ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት አሰራርን ይፋ አደረገ

121

ሐምሌ 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት አሰራርን ዛሬ ይፋ አድርጓል።

በአገልግሎት ማስጀመሪያ መርሐግብሩ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የኢኖቬሽን ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላን ጨምሮ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።

በዚህ ወቅት የኤሌክትሪክ አሰራሩ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ባለሙያዎች ትብብር የለማ ነው ተብሏል።

አሰራሩ በሚኒስቴሩ የሚሰጡ 10 አገልግሎቶችን በኦንላይን ማግኘት የሚያስችል ሲሆን በአማርኛና እንግሊዘኛ ቋንቋ አገልግሎት ያቀርባል ነው የተባለው።

ደንበኞች www.eservices.gov.et በሚለው ገብተው አገልግሎት ማግኘት የሚችሉ ሲሆን በአሰራሩ አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ 25 የመንግስት ተቋማት ዝርዝር መሀከል በአገልግሎት፣ በአገልግሎት አቅራቢ አሊያም በርዕስ ማግኘት የሚፈልጉትን አገልግሎት መምረጥ ይችላሉ ተብሏል።

በተጨማሪም ለተገልጋዮች አዋጭ ዘርፉን ለመለየትና ለመገናኛ ብዙሃን የአምራች ዘርፉን መረጃ ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል የኢንዱስትሪ መረጃ ስርዓትም በዛሬው እለት አስጀምሯል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በወቅቱ እንዳሉት፤ አሰራሩ ግልጽ፣ ተደራሽ፣ ወጪ ቆጣቢና ከብልሹ አሰራር የፀዳ አገልግሎት ለደንበኞች ለመስጠት ያስችላል።

የዲጂታል አሰራር ስርዓቶቹ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አካል የሆኑና በሚኒስቴሩ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በተቀላጠፈ መልኩ መስጠት የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል።

የኢኖቬሽን ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ በበኩላቸው የመንግስት አገልግሎቶችን በአይሲቲ መደገፍ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ እንዳለው በመገንዘብ ተቋማት አገልግሎታቸውን ዲጂታላይዝ እንዲያደርጉ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ በኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት እስካሁን 25 የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት 309 የለሙ የመንግስት አገልግሎቶችን ለደንበኞች እንዲሰጡ አስችሏል ብለዋል።

በመድረኩ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት ተደጋግፈው መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ይፈራረማሉ ተብሎ ይጠበቃል።