የአማራ አቀፍ የባህል ፌስቲቫል ለአንጋፋና ወጣት አርቲስቶች የገንዘብና የእውቅና ሽልማት በመስጠት ተጠናቀቀ

105
ባህር ዳር ግንቦት 10/2010 በባህር ዳር ከተማ ላለፉት አምስት ቀናት  የተካሄደው አማራ አቀፍ የባህል ፌስቲቫል ለአንጋፋና ወጣት አርቲስቶች የገንዘብና የእውቅና ሽልማት በመስጠት ተጠናቀቀ። ፌስቲሉ የከልሉን እምቅ የባህል ሃብት የጋራ ለማድረግ ያስቻለ እንደነበርና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል። ፌስቲቫሉ ትናንት ማምሻውን  ሲጠናቀቅ በክብር እንግድነት የተገኙት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ብናልፍ አንዱዓለም  እንደገለጹት ፌስቲቫሉ በክልሉ ውስጥ ያሉትን እምቅ የባህል ሃብቶች አጉልቶ ለማውጣትና የጋራ ለማድረግ ያስችላል። የክልሉ መንግስት የክልሉን እምቅ የባህል ሃብት ተወራራሽና በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የታወቁ እንዲሆን ይሰራል። ፌስቲቫሉ አራት አንጋፋ የኪነ-ጥበብ ሰዎችን የገንዘብና የእውቅና ሽልማት በመስጠት የህይወት ዘመን ተሸላሚ ያደረገ ሲሆን  አራት የኪነ-ጥበብ ሰዎች ደግሞ የማበረታቻና የእውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። የህይወት ዘመን ተሸላሚዎቹ 20 ዓመትና ከዚያ በላይ ከክልሉ አልፎ  በመላ አገሪቱና በተለያዩ አገራት በመዘዋወር በኪነ-ጥበቡ ዘርፍ  ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ናቸው። ተሸላሚዎቹ ተወዛዋዥ ሂሩት ኃይለማርያም፣ ማሲንቆ ተጨዋችና ድምጻዊ የኋላ ይመር፣ ድምፃሚ ያሲን ሞሀመድና ተወዛዋዥና ኪሮግራፈር አርቲስት ወርቁ ይማም ሲሆኑ ለእያንዳንዳቸው የ 50 ሺህ ብርና የህይወት ዘመን የምስክር ወረቀት ተሸላሚ ሆነዋል። በኪነ-ጥበብ ዘርፍ የክልሉን በሀል ከማሳወቅ ባለፈ  ለአገሪቱ የኪነ-ጥበብ እድገት  ከፍተኛ ስራ እየሰሩ የሚገኙ አራት አርቲስቶች ደግሞ የእውቅናና የማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት ተሰጥቷቸዋል። ተሸላሚዎቹ  አዝማሪ አማረ ሰለፈ፣ ተዋናኝ አህመድ አንሷር፣ ሰዓሊ ሙሉ ጌታ አባተና  ደራሲ ጥላሁን ጎሹ ናቸው። ለእያንዳንዳቸውም የ 20 ሽብርና የእውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። የህይወት ዘመን ተሸላሚ አርቲስት ወርቁ ይማም  የተሰጠው ሽልማት  ልዩ ስሜት እንደፈጠረበት ገልጾ  ወጣት አርቲስቶች እንዲበረታቱ እንዲህ አይነት ሽልማት ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚገባ ጠቁሟል። “ሰርተን  እንዳልሰራን፣ደክመን እንዳልደከምን  አስተዋሽ አጣን ብለን በተቀመጥንበት ሰዓት ይች ቀን ልዩ ቀኔ ናት” ሲል ገልጿል አርቲስት ወርቁ ። ብዙ የክልሉና የአገር ባለውለታዎች ስላሉ እየፈለጉ ማስታወስ ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚገባም ጠቁሟል፡፡ በፌስቲቫሉ ላይ ከተገኙ 14 የሙዚቃና 14 የትያትር  የባህል ቡድኖችም ከአንድ እስከ ሦስት ደረጃ ለያዙት የማበረታቻና የገንዝብና  ሽልማት ተስጥቷቸዋል። በሙዚቃ የባህል ውድድር ጎንደር ከተማ፣ ሰሜን ወሎና  ዋግምኸራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን በተከታታይ ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል፡፡ በትያትር የባህል ውድድር ደግሞ ማዕከላዊ ጎንደር ዞን፣ ጎንደር ከተማና ምእራብ ጎጃም ዞኖች ከአንድኛ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ አጠናቀዋል። ፌስቲቫሉ በየብሄረሰቦች እጅ ያሉ ባህሎችን ለማወቅና ጠንክሮ ለመስራት በግብዓትነት የሚያገለግል እንደሆነ ከምዕራብ ጎጃም ዞን ዋሸራ የባህል ቡድን የመጣው ወጣት  ላቀው ንጉሴ ገልጿል። በቡድኖች መካከል የነበረው ውድድር ጠንካራ እንደነበር አስረድቶ ፌስቲቫሉ በየዓመቱ መከበሩ ቡድኖች ለአሸናፊነት እንዲሰሩና ልምድ እንዲለዋወጡ አስችሏል ። ክልላዊ የባህል አንድነት እንዲኖርም አስተዋጽኦው የጎላ እንደነበረ ነው ያስረዳው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም