ለምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ዘላቂ ሰላምና የልማት ስኬት የንግዱ ማህበረሰብ አጋዥ መሆኑን በተግባር ማሳየት አለበት-ፕሬዝዳንት ሣኅለወርቅ

83

ሐምሌ 26 ቀን 2014(ኢዜአ) ለምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ዘላቂ ሰላምና የልማት ስኬት የንግዱ ማህበረሰብ አጋዥ መሆኑን በተግባር ማሳየት አለበት ሲሉ ፕሬዝዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ የቀድሞ መሪዎች በበላይነት የሚመሩትና በኢትዮጵያና በኢጋድ ቀጣና ሰላምና ልማት ላይ የሚንቀሳቀስ ፎረም በይፋ ሥራ ጀምሯል።

በዚሁ መርሐግብር ላይ የተገኙት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት ያጋጠሙ ግጭቶችና ጦርነቶች የንግዱ ማህበረሰብ ዋነኛ ሰለባ በመሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የንግዱ ማህበረሰብ ለሰላም መስፈንና ለህዝብ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በንቃት ሊሳተፍ ይገባል ብለዋል።

ሥራውን በይፋ የጀመረው ፎረምም በአስፈላጊ ወቅት መመስረቱን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ ራሷን ችላ እንድትቆምና ለኢጋድ ቀጣና እና ለአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም የሚጠበቅብንን ሥራ ባለማከናወናችን ብዙ ጉዳት አስተናግደናል ያሉት ፕሬዚደንቷ፤ በኡሁኑ ወቅት መንግሥት የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና የንግዱ ማህበረሰብ ተሳታፊ የሚሆኑበት ሁሉን አቀፍ የሰላምና የልማት ጥረቶችን እያደረገ ነው ብለዋል።

በኢጋድ ሀገራት ያሉ የደህንነት ስጋቶችን ተከትሎ የሚመጡ የድርቅና የልማት ትግብራ መስተጓጎሎችን ለማረም ፎረሙ ስትራቴጂ በመንደፍ መስራት እንደሚገባውም ጠቁመዋል።

በዚህም ኢትዮጵያና የኢጋድ ቀጣና ከግጭትና ጦርነት አዙሪት እንዲወጡ ለማስቻል ፎረሙ ስትራቴጂዎችን በመቀየስ ከአባል ሀገራት መንግሥታት ጋር በትኩረት እንዲሠራ ጠይቀዋል።

በሰላምና ልማት ዙሪያ ከሚሰሩ ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እንዲሠራ አሳስበው መንግሥት ለፎረሙ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የምትሻውን ዘላቂ ሠላም እውን ለማድረግ ልጆቿ እጅ ለእጅ ተያይዘው ከተነሱ በአጭር ጊዜ ማሳካት እንደሚቻልም ፕሬዝዳንቷ ጠቁመዋል።

የአንተርፕረነሪያል ፎረም ፎር ፒስ ኤንድ ዴቬሎፕመንት የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ሙላቱ ተሾመ፤ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ በተፈጠሩ ችግሮች የንግዱ ማህበረሰብ ዋነኛ ገፈት ቀማሽ ሆኗል ብለዋል።

የንግዱን ማህበረሰብ በማስተባበር ፎረሙ በኢትዮጵያና በቀጣናው ሀገራት ያሉ ግጭቶ በሰላማዊ አማራጭ እንዲፈቱ፣ ግጭቶች እንዳይከሰቱ መከላከል ከተከሰቱም በኋላ ፈጣን መልሶ ማቋቋም በማከናወን የኢኮኖሚና ማህብራዊ ልማት ሥራዎችን በመደበኛነት ለማስቀጠል በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት።

የፎረሙ ጠቅላላ ጉባኤ ሊቀመንበር አቶ በላይነህ ክንዴ፤ አሁን ያለንበት ሀገራዊ ሁኔታ የንግዱ ማህበረሰብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለሰላም ዘብ እንዲቆም ያስገድደዋል ብለዋል።

በመሆኑም መንግሥትና ህዝብ በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እንዲሁም ልማት እንዲረጋገጥ እያደረጉ ባሉት ጥረት የንግዱ ማህብረሰበ በባለቤትነት ለመሳተፍ በቁርጠኝነት መነሳቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም