የፌደራል ፍርድ ቤቶች በነሐሴ ወር መደበኛ የዳኝነት አገልግሎታቸውን መስጠት እንደሚቀጥሉ ተገለጸ

209

ሐምሌ 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) የፌደራል ፍርድ ቤቶች ከነሐሴ 01 እስከ 30 ቀን 2014 ዓ.ም መደበኛ የዳኝነት አገልግሎታቸውን መስጠት እንደሚቀጥሉ  የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

በ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት በሶስቱም የፌደራል ፍርድ ቤቶች ከ176 ሺህ በላይ መዛግብት እልባት ማግኘታቸውን አመልክቷል።

በፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/13 አንቀፅ 38(2) መሰረት የፌደራል ፍርድ ቤቶች ከነሐሴ 01 እስከ መስከረም 30 ባለው ጊዜ ዝግ እንደሚሆኑ ይደነግጋል፡፡

በዚህ ጊዜ ውስጥ ዳኞች ባላቸው የትርፍ ጊዜ አስቸኳይ የሆኑ ጉዳዮችን ብቻ ሊያስተናግዱ እንደሚገባም አዋጁ ያስቀምጣል፡፡

በ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት በዳኝነት አገልግሎቱ የታዩ አዎንታዊ ውጤቶችን ለማስቀጠል፣ ወደ 2015 ዓ.ም የሚያልፉ መዝገቦችን ቁጥር ለመቀነስ፣ የበሰሉ መዝገቦችን እልባት ለመስጠት እንዲሁም እስረኛ ያለባቸውን መዝገቦች ቅድሚያ ሰጥቶ ለመስራት እንዲያስችል በዳኞች ፈቃደኝነት ላይ በመመስረት የፌዴራል ፍርድ ቤቶቹ ከነሐሴ 01 እስከ 30 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ መደበኛውን የዳኝነት አገልግሎት መስጠታቸውን  እንደሚቀጥሉ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታውቋል።

የፌደራል ፍርድ ቤት ዳኞች ያላቸውን የእረፍት ጊዜ መስዋዕት በማድረግ መደበኛ የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት ፍቃደኛ በመሆናቸው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ምስጋናውን ያቀረበ ሲሆን ተገልጋዩም በዚህ አግባብ የፍርድ ቤቶቹን አገልግሎት ማግኘት  እንደሚችል አስታውቋል።

የፌደራል ፍርድ ቤቶች ማለትም የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ፤ ከፍተኛ እና ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት በሕገ-መንግስት እና በሕግ የተጣለባቸውን የዳኝነት አገልግሎቶችን ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡

በዚሁ መሰረት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 209 ሺህ 317 የሚሆኑ መዛግብት በሶስቱም የፌደራል ፍርድ ቤቶች ቀርበው 176 ሺህ 797 ለሚሆኑ ጉዳዮች እልባት ማግኘታቸውንና  ከሰኔ ወደ ሐምሌ  ወር የተላለፉ  32 ሺህ 520 መዛግብትም በመታየት ላይ እንደሚገኝ ፍርድ ቤቱ ባወጣው መግለጫ ገልጿል።