ተስፋ አስቆራጭ ፈተናዎች ቢኖሩም ተጨባጭና ለምስጋና ምክንያት የሚሆኑ ስኬቶች ተመዝግበዋል-ምእመናን

162

ሀዋሳ (ኢዜአ) ሐምሌ 25/2014- ተስፋ አስቆራጭ ፈተኛዎች ቢኖሩም ተጨባጭና ለምስጋና ምክንያት የሚሆኑ ስኬቶች ተመዝግበዋልሲሉ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ምዕመናን ተናገሩ።

ተስፋ የሚያስቆረጡ ፈተናዎችን በድል በማለፍ ለእዚህ ያበቃንን ፈጣሪ ልናመሰግን ይገባልም ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ታመስግን መርሃ ግብር አመስጋኝ ትውልድ ለመፍጠር ወሳኝ በመሆኑ ሊለመድ እንደሚገባም ምዕመናኑ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርቲያን መካነ ኢየሱስ የሀዋሳ እናት ማህበረ ምዕመናን የ”ኢትዮጵያ ታመስግን” መርሃ ግብርን አካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ ምዕመናኑ ለሀገር ሰላምና ልማት መጠናከር ለፈጣሪያቸው ጸሎትና ምስጋና አድርሰዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርቲያን መካነ ኢየሱስ የሀዋሳ እናት ማህበረ ምዕመናን አገልጋይ ቄስ ስምኦን ሞቻ “የምስጋና ቀን በመንግስት ደረጃ መታወጁ ተገቢና የኢትዮጵያ ቀዳሚ የሃይማኖት ባለቤትነት የሚያሳይ ነው” ብለዋል።

“ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ብትሆንም የፈጣሪ እርዳታ ባይበዛ ኖሮ ችግሩን አናልፍም ነበር” ብለዋል።

ችግሮችን በመቋቋም ያሳለፈንን ፈጣሪ ስናመሰግን ወደልቦናችን በመመለስና የፈጣሪን ባህሪ በመላበስ መሆን እንዳለበትም ጠቁመዋል።

“መነሻችንን ካወቅን መድረሻችንን እናውቃለን” ያሉት ቄስ ስምኦን፣ ኢትዮጵያ ቀድማ የተመረጠች የራሷ ታሪክ ያላትና አንድነትንና ስልጣኔን ለዓለም ያስተማረች መሆኑን አስታውሰዋል።

ዛሬም የብልጽግና ግብ በማስቀመጥ ተምሳሌት ለመሆን እየሠራች በመሆኑ አንድነትን በማጽናት ቀን ከሌሊት ለሥራ መትጋት እንደሚገባ አመለክተዋል።

የማህበረ ምዕመናን የወንጌልና ቲኦሎጂ ዘርፍ ሃላፊ ቄስ ደስታ ዳርዛ በበኩላቸው፣ “ኢትዮጵያዊያን በእርስ በርስ ግጭቶች፣ በበሽታ፣ በረሃብና በሌሎች ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ጉዳት ቢደርስብንም በፈጣሪ እርዳታ በመቆየታችን ብቻ ልናመሰግን ይገባናል” ብለዋል።

“በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ሀገርን በጽናት በማቆየት የነገን ተስፋ እንድናይ ያደረጉ መሪዮቻችንንም ልናመሰግን ይገባናል” ብለዋል።

“ተስፋ ቆርጠን ያለፍንባቸውን ጊዜያት ዛሬ ላይ ሆነን በማሰብ ማመስገን ነገን በተስፋ አሻግረን እንድናይ ያደርጋል” ሲሉም አክለዋል።

እርስ በርስ መመሰጋገን፣ መከባበርና መቻቻልን በማጠናከር ለሰላም ግንባታ ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ቄስ ደስታ፣ በተለይ ትውልዱ ከማማረር ወጥቶ ምስጋናን ባህሉ እንዲያደርግ መክረዋል።

ወንጌላዊ ዶክተር ተስፋዬ በላቸው በበኩላቸው ምስጋና ወደፈጣሪ የሚያቀርብ በመሆኑ ቂምና በቀል ባረገዘ ልብ መከናወን እንደሌለበት ተናግረዋል።

ምስጋና አጠገብ ካለ ሰው ጋር በመከባበር፣ ሰላምና ፍቅርን በመስጠት የሚከናወን ተግባር መሆኑንም ገልጸዋል።

“በመሆኑም ለአምላክና በአጠገባችን የተሻለ ለሰራ ምስጋና ማቅረብ ማህበራዊ መስተጋብራችን በመከባበር ላይ የተመሰረተና ጠንካራ እንዲሆን ያደርገዋል” ብለዋል።

“ያለውን ረስቶ የሚያማርር በራስ ላይ አደጋን ይጠራል” ያሉት ወንጌላዊ ዶክተር ተስፋዬ፣ “አመስጋኝ መሆን ጭንቀትን የማስወገድና ጤነኛ ግንኙነትን የመፍጠር አቅም ስላለው ማህበረሰቡ እንዲያጠናክረው አስገንዘበዋል።

የማህበረ ምዕመናን የሽማግሌዎች አስተዳደር ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አንተነህ ሰብስቤ በኩላቸው፣”ተስፋ አስቆራጭ ፈተኛዎች ቢኖሩም ተጨባጭና ለምስጋና ምክንያት የሚሆኑ ስኬቶች ተመዝግበዋል” ብለዋል።

የታላላቅ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ኢትዮጵያ ነገ ላይ የተሻለ ተስፋና የሚሰራ እጅ እንዳላት የሚያሳዩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

“ለዚህ ስኬት ያበቃንን ፈጣሪ እና በችግር ጊዜ ተስፋ ሳይቆርጡ በመስራት የልማት ጭላንጭል ያሳዩንን መሪዎችና መንግስትን ማመስገን መልካም በመሆኑ ልምድ ልናደርገው ይገባል” ሲሉም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ታመሰግን መርሃ ግብር በሀዋሳ ከተማና በዙሪያዋ ባሉ ከ20 በላይ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ማህበረ ምዕመናን መከናወኑን ታውቋል።

መርሃ ግብሩ አመስጋኝ ትውልድ መፍጠር ወሳኝ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ምዕመናኑ ገልጸዋል።