ከስሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከል በሚወጡ ምርጥ ዘሮች ምርታማ ሆነናል…. በሰሜን ወሎ ዞን ተጠቃሚ አርሶ አደሮች

3822

ወልድያ ግንቦት 10/2010 ከስሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከል የሚወጡ የተለያዩ ምርጥ ዘሮች ምርታማነታቸውን ከእጥፍ በላይ ለማሳደግ እንዳስቻላቸው በሰሜን ወሎ ዞን ተጠቃሚ አርሶ አደሮች ገለጹ።

በዞኑ ጉባ ላፍቶ ወረዳ ቀበሌ 11 የሚኖሩት አርሶ አደር ካሳ ከተማ ለኢዜአ እንደገለጹት ቀደም ሲል የአካባቢውን የጤፍ ዘር ሲጠቀሙ በሄክታር ከ10 ኩንታል በላይ ምርት አግኝተው አያውቁም ነበር።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከምርምር ማዕከሉ የወጣውን የቁንጮ ጤፍ መጠቀም መቻላቸው የሚያገኙትን የጤፍ ምርት በእጥፍ በማሳደግ ከ20 ኩንታል በላይ እንዳደረሰው ገልፀዋል።

በራያ ቆቦ ወረዳ የቀበሌ 07 ነዋሪ አርሶ አደር መንገሻ አያሌው በበኩላቸው አካባቢው ዝናብ አጠር በመሆኑ በአጭር ጊዜ የሚደርስና ድርቅን የሚቋቋም “ጊራና አንድ” የተባለውን የማሽላ ዝርያ በመጠቀም ምርታቸውን መሳደግ እንደቻሉ ተናግረዋል።

ቀደም ሲል “ደጋሌት” የተባለውን የማሽላ ዝርያ በመጠቀም በሄክታር እስከ 28 ኩንታል ምርት ያገኙ እንደነበር አስታውሰው፣ ዝርያው ተዘርቶ ለመድረስ ሰባት ወራት ከመቆየቱ ባለፈ ድርቅን የመቋቋም አቅም እንደሌለው ገልፀዋል።

” ጊራና አንድ ” የተባለው ማሽላ በአምስት ወራት የሚደርስና ድርቅን የሚቋቋም ከመሆኑ በተጨማሪ በሄክታር ከ38 ኩንታል በላይ ምርት እያገኙበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

“ቦሰት” የተባለው ምርጥ የጤፍ ዝርያ በ70 ቀናት ውስጥ ለምርት እንደሚደርስና በሄክታር 20 ኩንታል ምርት እያገኙበት መሆኑን የገለጹት ደግሞ በጉባላፍቶ ወረዳ የቀበሌ 04 ነዋሪ አርሶ አደር መኮንን አሊ ናቸው፡፡

በራያ ቆቦ ወረዳ የቀበሌ 07 የመስኖ ሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ዮሐንስ ቢምረው በበኩላቸው ከስሪንቃ ግብርና ምርምር ጋር በጋራ በመስራት ለገበሬው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዋወቅና ለማስፋት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የስሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር አረጋ ጋሻው ማዕከሉ ዝናብ አጠር ለሆነው ምስራቅ አማራ ተስማሚ ዝርያዎችን በምርምር በማውጣት ተጠቃሚ እያደረገ ነው።

ከእዚህ በተጨማሪ ከሌላ አካባቢ የወጡ ተስማሚ የሆኑ ዝርያዎችን በማላመድ እንዲሁም መስራች ዘር በመስጠት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

ዶክተር አረጋ እንዳሉት፣ ባለፉት 13 ዓመታት ማዕከሉ ባደረገው እንቅስቃሴ በሄክታር ከ23 እስከ 72 ኩንታል ምርት መስጠት የሚችሉ 13 ዓይነት የማሽላ ዝርያዎችን በምርምር በማውጣት ለአርሶ አደሩ አሰራጭቷል።

እንዲሁም ድርቅን ተቋቁመው ከ20 እስከ 22 ኩንታል ምርት የሚሰጡ ሰባት ምርጥ የጤፍ ዝርያዎች እንዲሁም በሄክታር በአማካኝ 36 ኩንታል ምርት የሚሰጡ ዘጠኝ የዳቦና የማካሮኒ የስንዴ ዝርያዎች በምርምር ወጥተው ተሰራጭተዋል ብለዋል፡፡

የምርምር ማዕከሉ በዚህ ዓመት 500 ኩንታል ምርጥ ዝርያዎችን አባዝቶ በቀጥታ ለአርሶ አደሩ ማሰራጨቱንም ዶክተር አረጋ አክለው ገልጸዋል፡፡

የስሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከል 100 ተመራማሪዎች ያሉት ሲሆን ከተቋቋመ ጊዜ አንስቶም በገብስ፣ በጥራጥሬ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በሌሎች ሰብሎች ከ60 በላይ በምርምር የተገኙ ዝርያዎችን ማሰራጨቱ ታውቋል።