በፖለቲካውና በልማቱ በመሳተፍ ለሀገሪቱ እድገት የድርሻቸውን እንደሚወጡ የኦነግ አመራርና አባላት ገለጹ

1274

መቀሌ መስከረም 5/2011 በፖለቲካውና ቀጣይ እድገት በሚያረጋግጡ የልማት ስራዎች ላይ በመሳተፍ ለሀገሪቱ እድገት የድርሻቸውን እንደሚወጡ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር/ ኦነግ/ አመራርና አባላት ገለጹ፡፡

የኦነግ አመራሮችና አባላት  መንግስት ያቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ በመቀበል ዛሬ በዛላአንበሳ ግንባር አድርገው መቀሌ ሲገቡ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

በአቀባበሉ ወቅት የድርጅቱ ማዕከላዊ ጦር አዛዥ አቶ በሪ ዋቄ ጋሪ እንዳሉት ከዚህ ቀደም ከድርጅቱ አመራሮች ጋር በተካሄዱት የውይይት መድረኮች በሰላማዊ መንገድ ትግላቸውን ለማካሄድ ስምምነት ላይ  ደርሰዋል፡፡

በዚህም ወደ ሀገር ቤት ለመግባት በወሰኑት መሰረት ከ1ሺህ 300 የሰራዊቱ አባላት ጋር መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ጥሪውን ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ከዛላአንበሳ ከተማ ነዋሪዎች ጀምሮ መቀሌ ለ እስኪደርሱ ድረስ ህዝቡ  ያሳያቸው መልካም አቀባበልና ፍቅር ሰራዊቱ አባላት ክብር የተሰማቸው መሆኑን  የጦሩ አዛዥ ገልጸዋል።

” በፖለቲካ ድርጅቶች መካከል የሃሳብ ልዩነት መኖር ለዴሞክራሲ ግንባታ አስፈላጊ በመሆኑ ሊጠላ አይገባውም ” ያሉት አዛዡ ሀሳብን በሰላማዊና በውይይት መድረክ ከመፍታት ይልቅ ወደ ጦርነት መሄድ ለሀገርም ለህዝብም እንደማይጠቅም አመልክተዋል፡፡

ወጣቱ ትውልድ ከስሜታዊነት ወጥቶ  ችግሮች አርቆ በማሰብና ሊፈታቸው እንደሚገባ ጠቅሰው ” አመራሮችም ወጣቱን ማዳመጥና ለሀገር እድገት የሚበጅ ሃሳብ እንዲያፈልቅ ማበረታታት ይገባቸዋል” ብሏል።

በድርጅቱ የሰራዊቱ አባል ሌንጮ ገዳ በበኩሉ በሀገሪቱ እየተካሄደ ባለው የዴሞክራሲ ግንባታ ውስጥ  የበኩሉን ሚና ለመጫወትና በልማቱ ዘርፍ ለመሳተፍ መወሰኑን ተናግሯል፡፡

በሰላማዊ መድረክ ሃሳብን ወደ ህዝብ ማቅረብና ህዝቡ ዳኛ በመሆኑ ተቀባይነትን ካላገኘ አሜን ብሎ መቀበል የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊለምዱት ይገባል ያለው ደግሞ ሌላው የድርጅቱ ሰራዊት አባል ኢቲቻ ጀቤሳ ነው፡፡

አመራሩና አባላቱ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ  ሃሳብን በነፃና በውይይት ለመፍታት ምቹ ሁኔታ በመፈጠሩ የትጥቅ ትግል ተመራጭ አይደለም፡፡

ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ እንቅስቀሴ ውስጥና  የልማት ስራዎች ላይ በመሳተፍ ለሀገሪቱ እድገት የድርሻቸውን እንደሚወጡ አመራርና አባላቱ ገልጸዋል።

የትግራይ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ረዳኢ ሓለፎም በበኩላቸው ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ ህወሓት ኦነግ ያካሄደውን እንቅስቃሴ በመደገፍ ያበረከተው አስተዋፅኦም ቀላል እንዳልነበረ አውስተዋል።

የኢትዮጵያ  ህዝቦች በመከባበር ላይ የተመሰረተ አንድነትና እኩልነት፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የዲሞክራሲያዊ ባህል እንዲዳብርና የሃሳብ ልዩነት በውይይት መፍታት የሰለጠነ አስተሳሰብ መሆኑም ገልጸዋል፡፡

የኦነግ አመራርና የሰራዊት አባላት  ወደ ሀገር ገብተው ሰላማዊ የትግል ስልት መምረጣቸው ትክክለኛ ውሳኔ በመሆኑ ምስጋናና እውቅና ሊቸራቸው እንደሚገባም ጠቁመዋል።