እኛ ኢትዮጵያውያን እጃችንን ለሽንፈት የማንዘረጋና ፈተናዎች የሚያጠነክሩን ህዝቦች መሆናችንን ታሪካችን ይመሰክራል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

97

ሐምሌ 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) እኛ ኢትዮጵያውያን እጃችንን ለሽንፈት የማንዘረጋና ፈተናዎች የሚያጠነክሩን ህዝቦች መሆናችንን ታሪካችን ይመሰክራል" ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኦሪገን በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አኩሪ ድል ላስመዘገቡ አትሌቶች የምስጋና መርኃ ግብር ትናንት ማምሻውን አካሂዷል፡፡

በመርኃ ግብሩ ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ ፣ የቀድሞ ታዋቂ አትሌቶች፣ የተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት በውድድሩ ለተሳተፈው የልዑካን ቡድን የ10 ሚሊየን ብር የገንዘብ ሽልማት አበርክቷል።

በተጨማሪም በውድድሩ የወርቅ፣ የብር እና የነሀስ ሜዳሊያ ላስገኙ አትሌቶች ውጤታቸውን መሰረት በማድረግ ከ500 እስከ 250 ካሬ ሜትር የሚደርስ የመሬት ስጦታ ተበርክቶላቸዋል ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ አትሌቶች ባስመዘገቡት ድል የኢትዮጵያን ክብር በዓለም አደባባይ ዳግም ከፍ አድርገዋል።

"እኛ ኢትዮጵያውያን እጃችንን ለሽንፈት የማንዘረጋና ፈተናዎች የሚያጠነክሩን ህዝቦች መሆናችንን ታሪክ ይመሰክራል " ሲሉም ነው የገለጹት፡፡

እልህ አስጨራሽ በነበረው ውድድር አትሌቶች የሀገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ  ላደረጉት አስተዋፅኦ ክብር ልንሰጣቸው ይገባል ብለዋል።

ማሸነፍ ከጥንት ጀምሮ የነበረ የኢትዮጵያዊያን መገለጫ መሆኑንም አስታውሰዋል ።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት  አትሌት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ በበኩሏ ለአትሌቶች ከሚሰጡ ስጦታዎች ሁሉ ውዱ ስጦታ ህዝብ የሚሰጠው ሞራል እና ክብር መሆኑን በመግለፅ በተደረገላቸው አቀባበል መደሰቷን ተናግራለች ።

በምስጋና መርሀ ግብሩ ላይ ተሳታፊ የነበረችው አትሌት ፋንቱ ሚጌሶ፤ የሀገራችን አትሌቶች ያገኙት ድል ኢትዮጵያዊያንን ያኮራ ውጤት ነው ስትል ገልፃለች።

ድሉ በትውልድ ቅብብሎሽ መቀጠል እንዳለበትም ነው የጠቀሰችው፡፡

የምስጋና መርሀ ግብሩ የተከናወነው "ሀገራችንን በዓለም አደባባይ ከፍ ስላደረጋችሁልን እናመሰግናችኋለን!" በሚል መሪ ሃሳብ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም