ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን የተተከሉትን በመንከባከብ የኢትዮጵያን የደን ሽፋን ወደነበረበት እንዲመለስ መሥራት ይገባል

175

ሀምሌ 22/2014/ኢዜአ/ ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን የተተከሉትን በመንከባከብ የኢትዮጵያን የደን ሽፋን ወደነበረበት እንዲመለስ መሥራት እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትላልቅ ፕሮጀክቶች ግምባታ ጽህፈት ቤት አመራሮችና ሰራተኞች ገለጹ፡፡

የጽህፈት ቤት ሰራተኞች ከአጋር አካላት ጋር በመሆን 13 ሺህ አገር በቀል ችግኞችን ተክለዋል፡፡

የጽህፈት ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ደቦ ቱንካ ተቋሙ ከሚያከናውናቸው የተለያዩ ትላልቅ ግንባታዎች በተጨማሪ ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ስኬት የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

የተቋሙ አመራሮችና ሰራተኞች በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የተከሏቸውን ችግኞች በቀጣይነት እንደሚንከባከቡ ገልጸዋል፡፡

የችግኝ ተከላው የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን በመቀነስ ረገድ ያለው አበርክቶ ከፍተኛ በመሆኑ ተቋሙ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣም ነው ያነሱት፡፡

በተጨማሪ የአፈር መሸርሸርን በመከላከል ለአካባቢ እና ለአፈር ጥበቃ የበኩሉን ይወጣል ነው ያሉት።

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር መስከረም ክንፈገብርኤል በበኩላቸው፤ ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን የተተከሉትን በመንከባከብ የኢትዮጵያን የደን ሽፋን ወደነበረበት እንዲመለስ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ጽህፈት ቤቱ ባለፈው ዓመት 20 ሺህ ችግኞችን መትከሉን በማስታወስ፤ የችግኞቹ የጽድቀት መጠን በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በመርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙ አጋር አካላት በበኩላቸው ችግኝ በመትከል ብቻ ሳይሆን በእንክብካቤውም ላይ በንቃት እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።

ከ6 ቢሊየን በላይ ችግኝ እንደሚተከልበት የሚጠበቀው አራተኛው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር እስከ አሁን ባለው ሂደት ከ5 ቢሊየን በላይ ችግኝ መተከሉን መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም