የኦሮሞ ወጣት ምርጫ የራሱን ባህልና ታሪክ እያሳደገ ከሌሎች ህዝቦች ጋር ሆኖ አገር መገንባት ነው - አስተያየት ሰጪዎች

89
አዲስ አበባ መስከረም 5/2011 የኦሮሞ ወጣት የራሱን ባህልና ታሪክ እያሳደገ ከሌሎች ህዝቦች ጋር ሆኖ አገር የመገንባት እንጂ ለግጭትና መከፋፈል በር ለሚከፍቱ ነገሮች ቦታ እንደማይሰጥ ኢዜአ ያነጋገረቸው አስተያየት ሰጪዎች ተናገሩ። ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የመጡና የአዲስ አበባ ወጣቶች፣ አዛውንቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በዛሬው እለት አዲስ አበባ ለገባው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አመራር ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል። በአቀባበል ስነስርዓቱ ላይ ከተገኙት መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው እንዳሉት፤ በአገሪቱ እንዲህ አይነት ዴሞክራሲያዊ ነጻነት እውን ሆኖ የሚወዱትን ድርጅት በደመቀ መልኩ በመቀበላቸው ተደስተዋል። ለዚህ አቀባበልም ከአዲስ አበባ እስከ 1 ሺህ ኪሎሜትር ርቀት ላይ ከሚገኙ ቦታዎች እንደመጡም ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የሚናገሩት። ከሃረርጌ በዴሳ የመጣው ሰበሃ አብዱልፈታ ይህን ቀን በማየቱና  ለዚህ በመድረሱ ደስተኛ   መሆኑን ገልጿል፡፡ “ለ27 አመታት ከአገራቸው  ተሰደው ለህዝባቸው  እንዲሁም ለኢትዮጵያም ህዝብ ነጻነት ከሃገር ወጥተዋል፤ በሰላም ወደ አገራቸውና ወገናቸው በመቀላቀላቸው መግለጽ የማልችለው ደስታ ነው እየተሰማኝ ያለው።’’  ያለችው ደግሞ ወጣት ሸምሲያ ሙሃመድ ከአዋሽ መልካሳ ናት፡፡ ወጣቱ በአሁኑ ወቅት የሚፈልገውም ከሌላው ህዝብ ጋር በመሆን አገር ለመገንባት፣ የሌላውን እያከበረ የራሱን ባህልና ወግ ለማሳደግ እንዲሁም ህይወቱን የመለወጥ ዓላማ ያለው መሆኑን በመግለጽ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ወጣቱ የመቻቻል ባህሉን የበለጠ እያዳበረ መሄድ እንደሚገባውም ጠቁመዋል። ወጣት ሸምሲያ ሙሃመድ እንዳለችው“ አገር ለመገንባት መጫወት ያለብን ሚና ቢኖር መጀመሪያ መቻቻል አለብን። ማንም ከማንም አይበልጥም አያንስምም ፤ ትንሹም ትልቁም ሰርተን ለአገራችን እድገትና ሰላም ማምጣት እንዳለብን ነው የማስበው።’’ “ወጣቱ ወደ ሁከት ወደ ብጥብጥ  ሳይገባ በመነጋገር ጥያቄም ካለው በሰላማዊ መንገድ መንግስትን በመጠየቅ ከመንግስት ጋር እጅና ጓንት ሆኖ መስራት አለበት፣ በኦሮሚያ ሁሉም ብሄርና ብሄረሰብ አሉ ከነሱም ተባብሮ አብሮ መኖር እንጂ መጣላት አያስፈልግም አንድ ሆነናል፣ በአንድነት እናምናለን።” ያሉት ደግሞ አቶ ግርማ ገላና  ከአዲስ አበባ ናቸው፡፡ ሼህ ሱሩር ከነገሌ ቦረና በበኩላቸው”እኔ ከዚህ በፊት የተጨቆንኩና የተበደልኩ ከሆንኩ ዛሬ መበቀል ሳይሆን ሁሉንም አቅፌ አብረን ከተፈጠርን ብሄረሰቦች ጋር ተቃቅፈን ለኦሮሞና ኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያንም እንደራሱ እንዲያለማ ለቄሮም ለሌላውም አደራ እላለው።” ብለዋል፡፡ በኤርትራ ውስጥ ሆኖ የትጥቅ ትግል ሲያካሂድ የቆየው ኦነግ ሰራዊትና አመራር አባላት በሰላማዊ ትግል ለመቀጠል ዛሬ ወደ አገር መግባታቸው ይታወቃል። የድርጅቱ መሪዎቹ አዲስ አበባ ሲገቡ በበርካታ ደጋፊዎቻቸው በመስቀል አደባባይ ደማቅ የሆነ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም