በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት የኮሚሽን ጅግጅጋ ቅርንጫፍ ስራ ጀመረ

1099

ጂግጂጋ መስከረም 5/2011 ኮሚሽኑ የጅግጅጋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በድጋሜ ስራውን መጀመሩን አስታወቀ፡፡

ከአንድ ወር በፊት በጅግጅጋ ከተማ በተከሰተው ሁከት ጉዳት ከደረሰባቸው  ተቋማት መካከል አንዱ  የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጅግጅጋ ቅርንጫፍ  ነው፡፡

የቅርጫፍ ጽህፈት ቤቱ ዋና ኮሚሽነር ጀማል መሀመድ ወርፋ ለኢዜአ እንደገለጹት  ጽህፈት ቤቱ በወቅቱ በደረሰበት ጉዳት አገልገሎቱን አቋርጦ ቆይቷል፡፡

በወቅቱ ሁከት ፈጣሪዎች በተቋሙ ላይ ጉዳት ያደርሱት ሰብዓዊ መብቶችን  የሚጥሱ አካላት ከህዝቡ የቀረበባቸው የቅሬታ ሰነዶች ለማጥፈት ነው፡፡

የኮሚሽኑ ባለሙያዎች በአካባቢው ሚረሚያ ቤቶች ይፈፀሙ የነበሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በማስረጃነት ያገኙባቸውን ሰነድ ለመሰወር  በቀድሞ የክልሉ አመራር ሆን ተብሎ  እንዲወድም መደረጉን  ኮሚሽነር ጀማል አስታውሰዋል፡፡

በክልሉ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ጥበቃ ለማጠናከር የኮሚሽኑ ጽህፈት ቤት በድጋሜ ስራ መጀመሩን የተናገሩት ኮሚሽነሩ ” የህግ የበላይነትና ሊያሰራን የሚችል የተሻለ የስራ ነፃነት አሁን በመፈጠሩ ወደ ተግባር መግባታቸውን አስታውቀዋል፡፡

በክልሉ  የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አስመልክቶ ያላቸውን ቅሬታ ዜጎች ያለምንም ፍርሃት ለተቋሙ ማቅረብ እንደሚችሉም አመልክተዋል፡፡

ከሚሽኑ በቀጣይም በሰብዓዊ መብት አያያዝ ለልዩ ፖሊስና ለሌሎች የፀጥታ አካላት የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሳዊ መብቶች በጥልቀት እንዲያውቁ ለማድረግ ከአሜሪካ ኢምባሲና ሌሎች ተባባሪ አካላት አንድ መቶ ሚሊየን ብር  ድጋፍ ማገኘታቸውን  ጠቅሰዋል፡፡

በክልሉ ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ታራሚዎች ማገኘት የሚገባቸውን አገልግሎት ፣ ያላቸው የሰብዓዊ መብት አያያዝ ለመፈተሽና ጥሰቶች ሲገኙም እንዲታረሙ  ኮሚሽኑ  በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡

አዲሱ የለውጥ አመራሩ ስራ ከጀመረ ወዲህ በክልሉ ይፈፀሙ የነበሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መቆማቸውን ያመለከቱት ኮሚሽነሩ ህዝቡ ከዚህ  አመራር ጋር በመተባበር  መብት ለማስከበር ድጋፉን እንዲሰጥ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡