በቁርጥ ቀን ጀግና አትሌቶቻችን ኮርተናል፤ ክብርና ልባዊ ምስጋና አቅርበናል ” የአፋርና ሀረሪ ክልሎች

385

ሰመራ /ሀረሪ ሀምሌ 21/2014 (ኢዜአ)- “ሰንደቅ ዓላማችን በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ባደረጋችሁ የቁርጥ ቀን ጀግና አትሌቶቻችን ኮርተናል፤ ክብርና ልባዊ ምስጋና አቅርበናል ” ብለዋል የአፋርና ሀረሪ ክልሎች፡፡

በአፋርና ሀረሪ  ክልሎች  ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ከፍ ላደረጉ ጀግኖች አትሌቶች የምስጋና መርሃ ግብር ዛሬ ተካሄዷል።

በአፋር ክልል ሰንደቅ አላማችን በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ላደረጉ ጀግኖች አትሌቶቻችን በተዘጋጀ የምስጋና መርሃ-ግብር ላይ የክልሉ ርእሰ-መስተዳድርን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሩና ሴክተር ቢሮ ሰራተኞች ተሳትፈዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአፋር ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶአወል አርባ  እንደገለጹት በአሜሪካ ኦሪገን  በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አትሌቶቻችን ታሪካዊና አኩሪ ድል አስመዝግበዋል።

“በዚህም ኢትዮጵያዊያን በዓለም አደባባይ አንገታችንን ቀና አድርገን እንድንሄድ፣ ሰንደቅ ዓላማችን በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ አድርገዋል” ብለዋል

“አትሌቲክስ ቡድኑ አባላት በዓለም አደባባይ ባሳዩት ኢትዮጵያዊ አንድነትና ሕብረት ኮርተናል” ብለዋል

“የቁርጥ ቀን ጀግና ለአትሌቶቻችን ለሀገራቸዉ ክብር ላደረጉት ከፍተኛ ተጋድሎ የአፋር ክልል መንግስትና ህዝብ ከፍተኛ ክብርና ልባዊ ምስጋና እናቀርባለን ” ሲሉም ገልጸዋል።

“የተገኘው ውጤት ከግለኝነት ይልቅ በቡድንና ህብረት ሀገርን ከፊት በማስቀደም የተገኘ በብዙ ችግር ውስጥ ላለው ሕዝባችንም አስተምህሮቱ ብዙ ነው” ሲሉ አመልክተዋል።

በአትሌቲክሱ መድረክ የተመዘገበው ውጤትም የኢትዮጵያን የከፍታ ጉዞ የሚያስቆም ምንም ሃይል እንደሌለ ማረጋገጫ መሆኑን አስታውቀዋል።

በስነ-ስርአቱ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና የሴክተር ቢሮ ሰራተኞች በተለያዩ መርሃ-ግብሮች ለአትሌቶቻችን ያላቸዉን ክብርና ልባዊ ምስጋና ገልጸዋል።


በተመሳሳይ “እንድ ሆነን እንስራ ኢትዮጵያ ታሸንፍ” በሚል መሪቃል በሀረሪ ክልል  ርእሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት በተከናወነው መርሃ ግብር የመንግስት ሰራተኞች፣ የከተማው ነዋሪዎች፣ የጸጥታ ሃይሎች እና የህብረተሰብ ክፍሎች ታድመዋል።

በመርሀግብሩ ላይ የተገኙት የሐረሪ ክልል የመንግስት ኮሙንኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ሄኖክ ሙሉነህ   ባስተላለፉት መልዕክት ድሉ ኢትዮዽያዊያን በችግር ውስጥ ማሸነፍ እንደምንችል ያሳየንበት ነው።

“አትሌቶቹ ውስጣዊና ውጫዊ ጫናን በመቋቋም  ያስመዘገቡት ድል  ኢትዮጵያንና መላው  ህዝቦቿን  አኩርቷል” ብለዋል።

የአትሌቶቹ ድልም  በሌሎች ተግባራት ላይ መነሳሳትን የፈጠረ መሆኑን ጠቁመው  የክልሉ ነዋሪም የተጀመሩ የልማትና የሰላም ስራዎች በትብብርና በመተጋገዝ ማጠናከር እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

“መርሀ ግብሩ  በዓለም አደባባይ የኢትዮጵያን አሸናፊነት ላሳዩ አትሌቶች ምስጋና የምናቀርብበት ነው” ሲሉም ተናግረዋል።