ዋልያዎቹ በቻን የእግር ኳስ ውድድር የደቡብ ሱዳን አቻቸውን 5ለ0 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ አለፉ

421

ሐምሌ 21 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋልያዎቹ) በአገር ውስጥ ሊግ የሚገኙ ተጫዋቾች ብቻ ለሚሳተፉበት የአፍሪካ እግር ኳስ ሻምፒዮና (ቻን) ከደቡብ ሱዳን ጋር ያደረገውን ጨዋታ 5ለ0 በማሸነፍ በተመሳሳይ ድምር ውጤት ወደ ቀጣዩ ዙር አለፉ።

ሰባተኛው የቻን የእግር ኳስ ውድድር እ.አ.አ በ2023 በአልጄሪያ አስተናጋጅነት ይካሄዳል።

ዋልያዎቹ ሐምሌ 15 ቀን 2014 ዓ.ም ከደቡብ ሱዳን ባደረጉት የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታ ያለ ምንም ግብ አቻ ቢለያይም በመልሱ ጨዋታ 5 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው ብሔራዊ ቡድን ባደረገው የመልስ ጨዋታ በረመዳን የሱፍ፣ አማኑኤል ገብረሚካኤል፣ መስዑድ መሐመድ፣ ይገዙ ቦጋለ እና ፒተር ሜከር (በራሱ ግብ ላይ) ባስቆጠሩት ግብ ዋሊያዎቹ አሸንፈው ወጥተዋል።

ዋልያዎቹ ወደ ውድድሩ ለማለፍ ከሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን ጋር የመጨረሻ የማጣሪያ ጨዋታቸውን እ.አ.አ 2022 ነሐሴ ላይ ያደርጋሉ።

ሰባተኛው የቻን የእግር ኳስ ውድድር እ.አ.አ 2023 ጥርና የካቲት ወራት በአልጄሪያ አስተናጋጅነት ይካሄዳል።

ውድድሩ እ.አ.አ ነሐሴ 2022 መካሄድ የነበረበት ቢሆንም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት መራዘሙ የሚታወስ ነው።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የተሳታፊዎች ቁጥር በመጨመር ከዚህ ቀደም በሻምፒዮናው የሚሳተፉ 16 አገራትን በአልጄሪያው ውድድር ወደ 18 ከፍ ማድረጉ ይታወቃል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤