ድርጅቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ኢንተርፕራይዞች የ12 ሚሊዮን ብር የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

81

ደሴሐምሌ 21/2014  (ኢዜአ)  የኔዘርላንድ የልማት ድርጅት ከማስተርካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር በአማራ ክልል በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ኢንተርፕራይዞች 12 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ቁሶችን ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉን በደሴ ከተማ ተገኝተው ያስረከቡት የድርጅቱ ተወካይ አቶ አክሊሉ ዲሮ እንደገለጹት፣ ድርጅቱ ሥራ አጦችን አደራጅቶ ስልጠና በመስጠት የሥራ ዕድል ይፈጥራል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ አካባቢዎች ከ121 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች በተለያየ መስክ የሥራ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል።

ይሁንና በጦርነቱ በርካታ ኢንተርፕራይዞች ውድመት ስለገጠማቸው የሥራ እድል የተፈጠረላቸው ወጣቶች ጭምር መልሰው ሥራ አጥ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የወደሙ ኢንተርፕራይዞች ቀድሞ ወደነበሩበት እንዲመለሱ መልሶ ለማቋቋም በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመው፣ በዛሬው ዕለት 12 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የተለያዩ ቁሶችን ለኢንተርፕራይዞቹ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

አቶ አክሊሉ እንዳሉት ከድጋፉ መካከል ውሃ መሳቢያ ፓምፕ፣ ጀነሬተር፣ የተለያዩ የአትክልትና ፍራፍሬ ዘር፣ የወተት መያዣ እንዲሁም ለዶሮ እርባታ የሚያገለግሉና ሌሎችም ቁሶች ይገኙበታል።

በዛሬው ድጋፍ በሰሜን ሸዋ፣ በደቡብና ሰሜን ወሎ ዞኖች እንዲሁም በደሴ ከተማ አስተዳደር በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው 381 ኢንተርፕራይዞች ተጠቃሚ እንደሚሆኑም አብራርተዋል።

ወጣቶቹ ከስነ ልቦና ጫና ተላቀው በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ እንዲገቡ ከስልጠና በተጨማሪ ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አመልክተዋል።

በድጋፍ ርክክቡ ላይ የተገኙት የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ተስፋዬ ዳኜ በጦርነቱ የበርካታ ኢንተርፕራይዞች ንብረት መዘረፉንና መውደሙን ጠቁመው፣ ኢንተርፕራይዞቹን መልሶ ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኔዘርላንድ የልማት ድርጅት ለ142 ኢንተርፕራይዞች 4 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር የሚገመት የተለያየ ቁሳቁስ ዛሬ ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመው፣ “ድጋፉ በከፊልም ቢሆን ወደሥራ ለማስገባት ያግዛል” ብለዋል።

በተለይ በመስኖ ልማት፣ በወተት ምርት፣ በደሮ እርባታና በሌሎችም የሥራ መስኮች ለተሰማሩ ኢተርፕራይዞች የሚያስፈልጉ ቁሶች በድጋፉ በመካተታቸው አመስግነዋል።

ጉዳት ለደረሰባቸው 40 ኢንተርፕራይዞች የሚሆን ድጋፍ በማግኘታቸው መደሰታቸውን የገለጹት ደግሞ የደሴ ከተማ አስተዳደር ስራና ስልጠና መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ዘይነባ ሁሴን ናቸው።

“ኢንተርፕራይዞቹ በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ከድርጅቱ ጋር በቅንጅት እንሰራለን፣ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትልም እናደርጋለን” ብለዋል።

“ያገኘነው ድጋፍ በከፊልም ቢሆን ወደስራ እንድንገባ እድል ስለሚሰጠን ድርጅቱን እናመሰግናለን” ያለው ደግሞ በደሴ ዙሪያ ወረዳ የቀበሌ 30 ነዋሪ ወጣት የሱፍ አሊ ነው።

ከአንድ ዓመት በፊት 64 ሆነው በመደራጀት ከመንግስት ባገኙት መሬት አትክልትና ፍራፍሬ የማልማት ሥራ መጀመራቸውን ጠቁሞ፣ በጦርነቱ ጀነሬቶሮቻቸውንና ሌሎችን መገልያዎችን በአሸባሪው ህወሓት መዘረፋቸውን አስታውሷል።

“ከኔዘርላንድ የልማት ድርጅት ዛሬ ባገኙት ጀኔሬተርና ሌሎች ተዛማች ቁሶች ተጠቅመን በቀጣይ ወደ ሥራ መግባት እንችላለን” ብሏል።

በድጋፉ ላይ የተለያዩ የሥራ ሃላፊዎች፣ ባለሙያዎች እና የኢንተርፕራይዝ ተወካዮች ተገኝተዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።