የሀገር አንድነት ማሳያ-አትሌቲክስ

283

ኢትዮጵያ በብርቅዬ እና አኩሪ ልጆቿ አመራር ሰጭነት፣ አሰልጣኝነት እና ታታሪ ተወዳዳሪነት ታግዛ ባለፉት 10 ቀናት በአሜሪካዋ ኦሪገን ከተማ በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር ላይ ደምቃ ሰንብታለች፡፡

እንቁዎቿ በሻምፒዮናው ላይ ባደረጉት እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ 4 ወርቅ፣ 4 ብር እና 2 ነሃስ በድምሩ 10 ሜዳሊያዎችን በማግኘት አሜሪካንን በመከተል እና በርካታ ሀገራትን በማስከተል ከዓለም በሁለተኛነት ከአፍሪካ ቀዳሚ ሆና አጠናቃለች፡፡

ህዝብ ማስተሳሰሪያ ገመድ-አትሌቲክስ

ውጤቱም የኢትዮጵያ ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክር አንዳች ገመድ በምትፈልግበት ወሳኝ ወቅት የተገኘ እና በብዝሃነት ውስጥ ያለን አንድነትያሳየ ነው፡፡

የሁልጊዜ ባለውለታ አትሌቶቿ ልክ እንደጥንቱ በዓለም መድረክ ከፍ እንድትል እና ክብር እንድትጎናጸፍ አድርገዋታል፡፡ በአሜሪካ ኦሪገን ከተማ የተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የተገኘው አስደናቂ ውጤት ኢትዮጵያውያን በመከባበር፣ በመተባበር እና በመደማመጥ ቢሰሩ የማያሳኩት ውጤት እንደሌለም ማሳያ ነው ፡፡ በሩጫው ዘርፍ በርካታ ክብረ-ወሰኖችን የግሉ ያደረገው  አትሌት ሻለቃ ሀይሌ ገብረስላሴ ከኢዜአ ጋር በነበረው ቆይታም ይህንንኑ መስክሯል፡፡

ጀግናዋ እና የምንግዜም የኢትዮጵያ ባለውለታ የሆነችው አትሌት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ  ውጤቱን የአዲስ ዓመት ስጦታ ገጸ-በረከት ብለዋለች፡፡ ድሉ በሌሎችም ዘርፎች መስራት ለምትፈልጋቸው ሀገራዊ ስራዎች ስንቅ እንደሚሆናት በስፍራው ለሚገኙ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ስትናገር ተደምጣለች።

የውጤታማነቱን ምስጢር ስትናገርም በቡድን የመስራት፣ የመተባበር እና የመከባበር ውጤት ነው። ለዚህም አትሌቶቹ፣ አሰልጣኞቹ፣ የህክምና ቡድኑ፣ የመገናኛ ብዙሃኑ፣ እና የአመራሩ ተናቦ የመስራት የታየበት ነው፡፡  

ብዙ ሆኖ እንደ አንድ የመስራት ውጤት

የአትሌቶቹ  የቡድን ስራ ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ ከተከባበርንና ከተዋደድን ሌላው እንደሚያከብረን እና እንደሚያቅፈን ያሳያል ይለናል ጀግናው አትሌት ሻለቃ ሀይሌ ገብረስላሴ ፡፡

መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም ከሚለያዩን ጥቃቅን ነገሮች ይልቅ አንድ በሚያደርጉን ግዙፍ ጉዳዮች ላይ በማተኮር በአንድነት ድህነትን ታግሎ መጣል ቀዳሚ ስራው አድርጎ ቢሰራ ታላቋን ኢትዮጵያ መገንባት እንደሚቻል የአትሌቶቻችን ትብብር አመላካች መሆኑን ያሰረግጣል፡፡ 

በየትኛውም የስፖርት ውድድር ላይ ትብብር፤ በትብብር ውሰጥ ደግሞ ፉክክር ያለ ነው፡፡ ይህ ጎልቶ ከሚታይባቸው ስፖርታዊ ውድድሮች መካከል ደግሞ አትሌቲክስ አንዱ ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም ይህንን ስፖርታዊ መርህ ጠንቅቀው በማወቅ ባለፉት በርካታ ዓመታት በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ላይ በመተግበር ለሀገራቸው አስደማሚ ውጤቶችን አስገኝተዋል፡፡ አሁን በኦሪገኑ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የተገኘውም ውጤት የዚሁ ስፖርታዊ መርህ ነጸብራቅ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በኦሪገኑ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር ላይ ያስመዘገበችው ውጤት በወንዶች ማራቶን በአትሌት ታምራት ቶላ ወርቅ እና በአትሌት ሞስነት ገረመው ብር፤ በሴቶች ማራቶን በአትሌት ጎተይቶም ገብረስላሴ ወርቅ፤ በ10 ሺህ ሜትር ሴቶች በአትሌት ለተሰንበት ግደይ ወርቅ፤ በሴቶች 5 ሺህ ሜትር በአትሌት ጉዳፍ ጸጋይ ወርቅ እና በአትሌት ዳዊት ስዩም ነሃስ፤ በሴቶች 3 ሺህ ሜትር መሰናክል በአትሌት ወርቅውሃ ጌታቸው ብር፣ በመቅደስ አበበ ነሃስ፤ በሴቶች 1500 ሜትር በአትሌት ጉዳፍ ጸጋይ የብር፤ በወንዶች 3 ሺህ ሜትር በአትሌት ለሜቻ ግርማ የብር፤ በአጠቃላይ 4 የወርቅ፣ 4 የብር እና 2 የነሃስ በድምሩ 10 ሜዳሊያዎችን ለሀገራቸው አምጥተዋል፡፡

በውጤቱም ኢትዮጵያ አሜሪካንን በመከተል እና በርካታ ሀገራትን በማስከተል ከዓለም በሁለተኝነት አጠናቃለች፡፡ ለአኩሪ ድሉ ብርቅዬዋ እና በኢትዮጵያዊነት መንፈስ የተለከፈችው ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉን ና የፌዴሬሽኑ አመራሮች አርዓያነት ለአዳዲስ አትሌቶች ጥንካሬን ፈጥሯል፡፡   

የተገኘው ውጤት ከግል ዝና እና ጥቅም ይልቅ የሀገር ጥቅም እና ድል እንደሚበልጥ ያስመሰከረ እና ሀገራዊ ስሜት በትልቁ የተንጸባረቀበት ውድድር እና ውጤት ነው፡፡ ውጤቱ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት በዝቅታ ውስጥ ከፍታ፤ በትብብር ውስጥ ድል መኖሩን በተጨባጭ ያሳየ ስለመሆኑም እንዲሁ እየተገለጸ ይገኛል፡፡

እልህ ምላጭ ያስውጣል እንደሚባለው ሀገራዊ ብሂል በአሜሪካ ኦሪገን ከተማ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያውያን ያስመዘገቡት ውጤት ቀደም ሲል በቻይና ቤጂንግ በተካሄደው የኦሎምፒክ ውድድር ላይ የተገኘው ዝቅተኛ ውጤት በቁጭት እንዲነሳሱ እንዳደረጋቸውም ተገልጿል፡፡ 

ለውጤቱ አመርቂ መሆን የጀግናዋ እና የወቅቱ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት እና የሀገር ፈርጧ የአትሌት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበር የስፖርት ተንታኙ መንሱር አብዱል ቀኒን ጨምሮ የስፖርቱ ዓለም ሰዎች ዘግበዋል፡፡

ለዚህም ለተወዳዳሪ አትሌቶች ስትሰጥ የነበረው ፍቅርና ክብር እንዲሁም ሙያዊ ድጋፍ እና አመራር የአትሌቶችን ጫማ ዝቅ ብላ እስከማሰር የደረሰ ትህትና እና ፍቅርን በምሳሌነት ይጠቅሳሉ፡፡

ጀግናዋ አትሌት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ ባለባት ሃላፊነት አመራር ከመስጠት ባለፈ የአትሌቶቹን ጭንቀት እንባ በማንባት ጭምር ስትጋራ እንደነበር የሚወጡት የምስል ማስረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ ለዚህም ውድድሮቹ በሚካሄዱበት ስፍራ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከሌሎች አትሌቶች ሲገጥማቸው የነበረውን እልህ አስጨራሽ ትግል በአሸናፊነት ለመወጣት እና ተጠባቂውን ድል ለማስመዝገብ ሲያርጉ በነበረው ግብ ግብ ውስጥ ራሷ ተወዳዳሪ እስክትመስል ድረስ ምን ያል በጭንቀት ስትዋጥ እንደነበር የሚያሳዩት ምስሎች ይጠቁማሉ፡፡ 

በአትሌቲክሱ መስክ የተገኘው አንጸባራቂ ድል በሌሎች ዘርፎችም በመድገም ሀገርን ከድህነት ማውጣት እንደሚቻል ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ለዚህም ሻለቃ አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ የድሉ ምስጢር የጋራ ስራ በመሆኑ በአትሌቲክሱ የተገኘውን ድል በሌሎችም በመድገም የጋራ ሀገርን ለመገንባት ልንጠቀምበት ይገባል ሲል አጽንኦት በመስጠት የተናገረው፡፡

ስፖርት ለሰላምና ለወንድማማችነት መጠናከር አስተዋጽኦው ከፍተኛ መሆኑን ከፋና ጋር በነበረው ቆይታ የተናገረው ሻለቃ አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ አሁን በሀገራችን የሚታዩትን ችግሮች ለመፍታትም ስፖርትን አንዱ የችግር መፍቻ ቁልፍ አድርጎ መጠቀም እንደሚገባ ምክረ-ሃሳቡን አቅርቧል፡፡

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ላይ በሰሩት የቡድን ስራ የኢኮኖሚ የበላይነት ካላቸው በርካታ ሀገራት በላይ የሆነ ውጤት ማስመዝገባቸው በሌሎችም ዘርፎች በትብብር እና በቅንጅት ቢሰራ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ጥሩ ማሳያ ነው ይላል ሀይሌ፡፡

ያለ ውድድር የአሸናፊነት መንፈስም ሆነ አሸናፊነት የማይገኝ በመሆኑ ልክ እንደ እንቁዎቹ አትሌቶቻችን ሁሉ ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፎች በዓለም አደባባይ አሸናፊ ለማድረግ ድር ቢያብር…እንዲሉ አበው ሁሉም ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያ የሚለውን ስም በጋራ ከፍ አድርጎ በመያዝና እንደ ብዙ ሰው ተናጋሪ እንደ አንድ ልብ መስካሪ በመሆን፣ የውድድር መርህን በማክበር እና የአሸናፊነት መንፈስን በመላበስ በትብብር በመስራት ሀገራችንን በጋራ እንገንባ መልዕክታችን ነው፡፡ በድጋሚ እንኳን ደስ አለን!!    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም