በኢትዮጵያ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ሂደት ወንጀለኞች ላይ የተጀመረው እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት- ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

91

ሐምሌ 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) "በኢትዮጵያ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ሂደት በአሸባሪዎችና ወንጀለኞች ላይ የተጀመረው ሕጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት" ሲሉ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛ ዲግሪ፣ በመጀመሪያ ዲግሪ፣ በዲፕሎማ እና ሰርተፊኬት 1 ሺህ 631 ተማሪዎችን አስመርቋል።

በምርቃቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ በአገሪቷ ሰላም እንዲሰፍንና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ በሽብርተኞች እና ወንጀለኞች ላይ የተጀመረው ህጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡

በሰላም መኖር የሁሉም ነገር መሰረት በመሆኑ ለዚህም ፖሊስ ሃላፊነቱን በብቃት ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበው ለዚህም ህብረተሰቡና ፖሊስ በወንጀል መከላከል የሚያደርጉትን ትብብር አጠናክረው መቀጠል አለባቸው ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ሰላም፣ ዕድገትና ልማትን በእጅጉ ትሻለች ያሉት ፕሬዚዳንቷ የተደቀኑባትን መሰናክሎች በማስወገድ ወደ ጀመረችው የአድገት ጎዳና መምራት ይገባል ብለዋል።

የዛሬ ተመራቂዎች በርካታ ውጣውረዶችን በማለፍ ለሌላኛው የሕይወት ምዕራፍ በመብቃታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ያሉት ፕሬዝዳንቷ ለዜጎች ደህንነት፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር በትኩረት እንዲሰሩ አሳስበዋል።  

"ህዝባችሁን በቅንነት በታማኝነትና በፍጹም አገር ወዳድነት ያለ አድሎ እንድታገለግሉ አደራ እላለሁ" በማለትም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።  

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል፤ በየጊዜው እየረቀቀ የሚሄደውን የወንጀል ድርጊት ለመከላከል የፖሊስ ብቃት እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

በዩኒቨርስቲው ለህዝቡ የሚመጥኑና ፖሊሳዊ ስነ-ምግባር የተላበሱ ባለሙያዎችን እያፈራ መሆኑን ጠቅሰው ተመራቂዎች ያገኙትን ሙያና ክህሎት በተግባር እንዲያውሉ አሳስበዋል።

የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን አበበ፤ የኒቨርሲቲው በዛሬው ዕለት በተለያዩ ሙያ የሰለጠኑ 1 ሺ 631 ፖሊሶችን ማስመረቁን ገልጸዋል፡፡

በየሚመደቡባቸው ተቋማት ፖሊሳዊ ሪፎርሙ ስራ ላይ እንዲውልና ውጤት እንዲያሥመዘግብ በማድረግ ተመራቂዎች ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።  

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ የተመሰረተበትን 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዩቤልዩ በዓል በተለያዩ መርሐግብሮች በማክበር ላይ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም