ሀገራችን ሁለንተናዊ እድገት እንድታስመዘግብ ተመራቂዎች የድርሻቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል- ዶክተር ታፈረ መላኩ

133

ደብረ ማርቆስ፤ ሐምሌ 16/2014(ኢዜአ) ''ተመራቂ ተማሪዎች ነገሮችን በአርቆ አሳቢነት በማየት ሀገራችን አሁን ከገጠማት ችግር ተላቃ ሁለንተናዊ እድገት እንድታስመዘግብ ሚናቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል '' ሲሉ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ታፈረ መላኩ አሳሰቡ።

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛ እና የመጀመሪያ ዲግሪ መረሃ ግብር ያሰለጠናቸውን 2 ሺህ 108  ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።

በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ ዶክተር ታፈረ መላኩ እንዳሉት፤  ኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርትን ጨምሮ በትምህርት ፍትሃዊነት እና ተደራሽነት እመርታዊ ለውጥ አስመዝግባለች።

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲም የዚሁ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዛሬ  በሁለተኛ እና በመጀመሪያ ዲግሪ ያስተማራቸውን 2ሺህ 108 ተማሪዎች ማስመረቅ መቻሉን አስታውቀዋል።

ተመራቂዎች በሰለጠኑበት የሙያ መስክ ከጠባቂነት ተላቀው ስራ ፈጣሪ ፤  በጥረታቸውና ጥንካሬያቸው ችግር ፈቺ መሆን እንዳለባቸው አመልክተዋል።

በሚሰማሩበት የስራ መስክ ሁሉ  ነገሮችን በአርቆ አሳቢነት  በማየት  ሃገራችን አሁን ከገጠማት ችግር ተላቃ ሁለንተናዊ እድገት እንድታስመዘግብ ሚናቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

የዕለቱ የክብር እንግዳ ፕሮፌሰር በላይ ካሳ  ባስተላለፉት መልዕክት፤  ከመማር የሚገኘው ትልቁ ነገር አለምን የተሻለ መኖሪያ ቦታ ለማድረግና እንዴት እንደምንጠቀምበት መገንዘብ መቻል መሆኑን ተናግረዋል።

መማርን የሰብዓዊ መሻሻል እና አዎንታዊ የለውጥ መሳሪያ አድርገን ማየት እና መቀበል ይጠበቃል ብለዋል።

ተመራቂ ተማሪዎችም ሀገራችሁን አለም ካለችበት የእድገት ማማ ለማድረስ ተወዳዳሪ እና ብቁ ዜጋ ለመሆን ጉዟችሁ ሳይገታ ካሰባችሁበት ለመድረስ የግል ጥረታችሁን ማጠናከር አለባችሁ ሲሉ ገልጸዋል።

የህግ ትምህርት ክፍል ተመራቂ  አለም ባንተ ይግዛው በሰጠው አስተያየት፤  በተማርኩት ሙያ ህግን መሰረት በማድረግ የህግ የበላይነትን ለማስከበር እሰራለሁ ብሏል ።

''በተመረቅኩበት ዘርፍ ስራ ጠባቂ ሳልሆን ስራ ፈጣሪ በመሆን ሳይማር ያስተማረኝን ማህበረሰብ ማገልገል የመጀመሪያ ዓላማዬ ነው'' ያለችው ደግሞ ከቴክኖሎጂ ትምህርት ክፍል ተመራቂ እመናት ዳኛው ናት።

የዛሬው ተመራቂዎች በመደበኛውና በማታው ክፍለ ጊዜ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ሲሆን፤ ከመካከላቸውም 750  ሴቶች እንደሆኑ ተገልጿል።

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ  ከተቋቋመ ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ ከ45 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አሰልጥኖ ማስመረቁንና በአሁኑ ወቅት የሚያስተምራቸው ከ29 ሺህ   በላይ ተማሪዎች እንዳሉት ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም