የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትንና የጥላቻ ንግግርን ለመቆጣጠር መገናኛ ብዙኃን በቅንጅት እንዲሰሩ ተጠየቀ

148

ሐምሌ 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት፤ የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትንና የጥላቻ ንግግር መስፋፋትን ለመቆጣጠር መገናኛ ብዙኃን ሙያዊ ሥነ-ምግባርን አክብረው በቅንጅት እንዲሰሩ ጠየቀ።

በምክር ቤቱ መተዳደሪያ ደንብና በግልግል ዳኝነት የአሰራር ስርዓት ዙርያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐግብር ተካሂዷል።

የምክር ቤቱ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አማረ አረጋዊ፤ የፕሬስ ነጻነት ለድርድር ሳይቀርብ ሙያዊ ስነ-ምግባርን በጥብቅ ማክበርና ተቋማቱን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ሚዲያው ራሱን እንዲቆጣጠር ይጠበቃል ያሉት ሰብሳቢው ለዚህም ምክር ቤቱ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከህዝብ፣ ከመንግስትና ሌሎች አካላት ቅሬታ ሲቀርብ ችግሩን ለመፍታት የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት በጋራ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

በተለይም የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትንና የጥላቻ ንግግር መስፋፋትን ለመቆጣጠር መገናኛ ብዙኃን ሙያዊ ስነ-ምግባርን አክብረው በቅንጅት እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

የምክር ቤቱ አባል ዶክተር ንጉሤ ተፈራ፤ ከለውጡ ወዲህ ለሚዲያው አመቺ የሆነ ሕግና የፓሊሲ ማዕቀፍ ተቀርፆ በመተግበር ላይ መሆኑን አንስተዋል።

ሆኖም የሀገርን አንድነት ከማስጠበቅና ጽንፍ የወጡ ችግሮችን ከመከላከል አንጻር በሚዲያው የተከናወኑ ተግባራት አመርቂ አይደሉም ብለዋል።

በተለይም ሰላምን ለመግንባትና የሐሰተኛ መረጃዎችን ስርጭት ለመቆጣጠር የሚያስችሉ አሰራሮችን ሚዲያዎች ብዙም ሲሰሩ አይታይም ነው ያሉት።

ሰላምን በዘላቂነት ለመግንባትና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የሚዲያ ባለሙያዎችን አቅም የሚያጎለብቱ ተግባራት ማከናወን አላባቸው ሲሉም ተናግረዋል።

የሚዲያውን ዘርፍ በሚመጥን መልኩ ጥናት በማካሄድና አጀንዳ በመቅረጽ ዘላቂ የሰላም ግንባታ ስራ መሰራት የኖርበታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት በ2003 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን 59  የሚዲያ ተቋማትን  በአባልነት አቅፏል።