"በጋራ መቆም፤የጥፋት መልዕክተኞችን ለመመከት ፍቱን መድሃኒት"

98

በመንግስቱ ዘውዴ (ኢዜአ)

ታሪክ እንደሚያስረዳን ኢትዮጵያውያን አገራዊ ሰላማቸውንና ሉዓላዊነታቸውን መቼም ለድርድር አቅርበው አያውቁም። ወደፊትም አያደርጉትም። እርስ በርሳቸው በውስጥ ጉዳይ ባልተስማሙበት ወቅት እንኳን የጋራ ጠላት ሲገጥማቸው ሆ ብለው ዘምተዋል። ጠላታቸውን ድል ነስተዋል። በዓለም ፊት አስደናቂ ታሪክ አስመዝግበዋል። በቅርቡ ከውስጥም ሆነ ከውጭ የተቃጡ ሰላም የማደፍረስ እንቅስቃሴዎችን ለመከላከል እና ሉዓላዊነታቸውን ለማስከበር እንደህዝብ የተደረጉ ትብብርችን በአብነት ማንሳት ይቻላል፡፡

አንዳንድ ተቀናቃኝ አገሮች እና ቡድኖች በሌሎች አገሮች ላይ “አለን” የሚሉትን ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የየአገሮቹን ውስጥ ሰላም ማወክን እንደ አንድ የእጅ አዙር ጦርነት ማካሄጃ ስልት ይጠቀሙበታል። ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውም ይኸው ነው፡፡

ምንም እንኳን ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን በማንበርከክ ፍላጎታቸውን ማሳካት እንደማይችሉ በውል ቢረዱትም ካለፉት ጊዜያት ይልቅ ጠንከር ያለ እንቅፋት ማስቀመጣቸው እውነት ነው። ይህንን ተግዳሮት በብቃት ለመመከት በጋራ እንደመቆም ፍቱን መድሃኒት የለም፡፡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ ቤልጅጌ በቅርቡ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ “ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የሆነ ‘የግራጫ ጦርነት’ ውስጥ መሆኗን ተገንዘቦ ለአገራዊ ድል በጋራ መቆም ብቸኛው አማራጭ ነው” ማለታቸው ለዚህ ነው።

ኢትዮጵያን የመሰለ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታላቅ ስም እና ዝና እንዲሁም አንጸባራቂ የነጻነት ታሪክ ያላትን አገር ቀርቶ በቅኝ ግዛት ስር የቆዩ አገሮችን ሉዓላዊነት ማስከበር በርካታ ፈተናዎች እንደሚኖሩት የዘርፉ ተመራማሪዎች ይገልጻሉ። እንዲህ ባሉ የችግር ጊዜያት ዜጎች በጋራ በመቆም ሰላማቸውን ከማስጠበቅ ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌላቸውም ያስረዳሉ። በዚህ ዙሪያ በስፋት እየሰሩ ካሉት የማህበረሰብ አንቂዎች መካከል ወጣቱ ሱሌይማን አብደላ ከኢዜአ ጋር በነበረው ቆይታ እንደገለጸው ሃገራችን የሚስተዋለውን ውስጣዊ ፈተና እና ውጫዊ ጫና አሸንፎ ለማለፍ በጋራ መቆም የግድ ነው።

በአገር ውስጥ ራሳቸውን የሽብር ቡድን አድርገው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች በውጭ አገሮች እንደሚደገፉ እና እንደሚመሩ ግልጽ ነው። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሚታየውን የጸጥታ ችግር የበለጠ ለማባባስ የሚሰሩ አገሮች በመኖራቸው “ለሉዓላዊነቷ መከበር የጋራ ሃላፊነት መውሰድ አለብን” ሲሉም ይመክራሉ።

አሁን በኢትዮጵያ ላይ በታሪካዊ ጠላቶች በግልጽ እና በእጅ አዙር ጦርነት የተከፈተባት እና ሰላም የማደፍረስ እንቅስቃሴዎች የሚደረግባት ኢኮኖሚያዊ እድገቷንና አካባቢያዊ ተጽዕኖዋን በመፍራት እንደሆነ በየጊዜው የሚወጡ ትንታኔዎች ያስርዳሉ። በመሆኑም በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም የማደፍረስ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሁሉን አቀፍ ርብርብ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ከሚጠቀሙባቸው ስልቶች መካከልም፤ በህዝቦች መካከል ያሉ ልዩነቶችን ከአውዳቸው ውጪ ብያኔ መስጠት፣ የተከሰቱ ጥቃቅን ችግሮች ማጉላት፣ የሀሰት መረጃዎች ማሰራጨት፣ በንጹሃን ላይ አሰቃቂ ጭፍጨፋዎች በመፈጸም ህዝብን ማስቆጣት፣ በህዝብ እና በመንግስት መካከል መተማመን እንዳይፈጠር የስህተት መረጃዎች በብዛት መልቀቅ፣ ህዝብን በመንግስት ላይ ለማሳመጽ ግልጽ ቅስቀሳዎች የማድረግና በመንግስት እና በህዝብ መካከል የጠበቀ ግንኙነት እንዳይኖር ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ አሻጥሮች በመፍጠር የኑሮ ውድነት እንዲንር የማድረግ፣ እነዚህንም በሚዘውሯቸው መገናኛ ብዙሃን በተደጋጋሚ ማቅረብ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

እነዚህ የሽብር ቡድኖች የሽብር ዕቅዳቸውን እና አገር የማፍረስ ውጥናቸውን እውን ለማድረግ በአገሪቷ ታሪክ በህዝብ ብዛት ቀዳሚ ከሆኑት ኦሮሞና አማራ እንዲሁም በሌሎች ህዝቦች መካከል ልዩነትን በመፍጠር የተለመደውን የከፋፍለህ ግዛ ስልታቸውን ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም በኢትዮጵያ እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮች በሙሉ ላለፉት 30 ዓመታት በየአካባቢው የቀበሯቸው ፈንጂዎች ውጤቶች ስለመሆናቸው ማስረጃዎቸ ያመለክታሉ። የዚህ ዓይነቶቹ የሽብር እንቅስቃሴዎች የመንግስትን ትኩረት በማዛባት፣ የደህንነት መዋቅሩ ትኩረቱን በግጭት ማርገብ ተግባራት ላይ ብቻ እንዲጠመድ ያለሙ ናቸው። በሌሎች የልማት ዘርፎች ላይ መዋል የሚገባውን ሀብት ለጊዜያዊ ማቋቋሚያ ለማዋል እንዲገደድም በር ይከፍታል። ይህም መንግስትም ተረጋግቶ የተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶችንና የልማት ስራዎችን እንዳያከናውን ያደርጉታል።

ይህን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር “በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደረጃ ስለ ሽብር ቡድኖቹ ሰፊ ጊዜ ወስዶ መወያየት ለሽብር ቡድኖቹ ብቻ ሳይሆን ለጠላቶቻችንም ድል ነው። እነሱም የሚፈልጉት ይህንኑ ነው። እኛ እንደ መንግስት የራሳችን የትኩረት አቅጣጫ እና አጀንዳ አለን “ ማለታቸው ከላይ የተጠቀሰውን ሀሳብ የሚያብራራም ነው። 

አሁን በኢትዮጵያ እየተፈጸሙ ያሉ የሽብር እና የግፍ ድርጊቶች በሙሉ ባለፉት ዓመታት አገሪቷ ስትመራበት የቆየው የተሳሳተ የፖለቲካ አካሄድ ውጤቶች ናቸው፡፡ ለዚህም ነው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ ቤልጅጌ  “በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች በጽንፈኞችና በሽብር ቡድኖች በንጹሀን ዜጎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ባለፉት በርካታ ዓመታት አብሮነት እንዲሸረሸርና ኢትዮጵያ እንድትኮስስ ታስቦ ሲሸረብ የቆየ የፖለቲካ ሴራ ውጤት ነው” ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጸም የሽብር ተግባር በውስጥ ከሃዲዎች ብቻ የሚፈጸም እንዳልሆነ እና ይልቁንም የታሪካዊ ጠላቶች እጅ በረጅሙ እንዳለበት ሲገልጹ፤ በተለያዩ “የአገራችን አካባቢዎች የሚስተዋለው የሰላም መደፍረስ ተራ የአገር ውስጥ ችግር ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ልማት የማይሹ የውጭ ሀይሎች ስውር እጆች አለበት” ብለዋል።

የገዛ አገራቸውን ለታሪካዊ ጠላቶች ጥቅም ማስጠበቂያ የመስዋዕት በግ አድርጎ ለማቅረብ ሌት ተቀን የሚለፉት “ነጻ አውጪ ነን” የሚሉ ስብስቦች፤ ነገ በታሪካዊ ጠላቶች ድጋፍ ዕድል ቀንቷቸው ስልጣን ላይ ቢወጡ አገሪቱን ለእነዚህ ጠላቶች አሳልፎ ከመስጠት ውጪ አንዳችም የኔ የሚሉት ፖለቲካዊ ግብ እና ዓላማ የሌላቸው መሆኑን ከእኩይ ተግባራቸው ለመገንዘብ እነሱን መሆን አይጠይቅም፡፡ ለዚህ ነው የውጭ ሀይሎችን አጀንዳ ከማስፈጸም ውጪ ይህ ነው የሚባል አገራዊ ግብ የሌላቸውን ተላላኪ ቡድንኖች እንደህዝብ በመነሳት “በቃ” መባል ያለበት ወቅት ላይ ደርሰናል የሚባለው፡፡ 

ለአገር ዘላቂ ሰላም ግንባታ መንግስት የአንበሳውን ድርሻ የሚወስድ ቢሆንም፤ በአንድ እጅ ማጨብጨብ እንደማይቻለው ሁሉ ለአገር ሰላም መረጋገጥ እያንዳንዱ ዜጋ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ የመገናኛ ብዙሃን እና ሌሎችም ከመንግስት ጋር በትብብር መስራት ይገባል፡፡ ይህን ለማድረግም “ዜጎች በሀሰተኛና የተዛባ መረጃ ሳይደናገሩ በመደማመጥ ለሰላምና አንድነት በጋራ መስራት አለባቸው” ሲሉ በርካቶች እየመከሩ ይገኛሉ   

ወቅቱ ታላላቅ አገራዊ ፕሮጄክቶች እውን የሚሆኑበት በመሆኑ ታሪካዊ ጠላቶች የፕሮጄክቶቹ  ሂደት ማስቆም እንደማይችሉ እርግጥ ሲሆንባቸው፤ የውስጥ ተላላኪዎችን በመጠቀም ይህን ለማደናቀፍና ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቷ እንዳትጠቀም ለማድረግ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያውያን በአንድነት በቆሙባቸው ጊዜያት ሁሉ ፈተናዎቻቸውን በድል መወጣታቸውን በማስታወስ በጋራ መቆም ለነገ የማይባል ተግባር  ነው።

እነዚህ ታሪካዊ ጠላቶች እና የውስጥ ከሃዲዎች “ኢትዮጵያን ማንበርከክ የሚቻለው የህዝቦቿን አንድነት በመሸርሸር ነው” የሚል አቋም ይዘው በጋራ በተጠና መልኩ እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ በውል መገንዘብ ይገባል። በብሄርና ሀይማኖት በመከፋፈል የርስ በርስ ግጭት ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ እንደቆዩት ሁሉ በቀጣይም መሰል ስልት እንደሚከተሉ ይታመናል፡፡ ኢትዮጵያውያን ከራስ በላይ ንፋስ እንደሚባለው ለአገር ሰላም እና ደህንነት ቅድሚያ በመስጠት ከመንግስት ጎን መቆም የህልውና መጠበቅ ቁልፍ ተግባራችን ልናደርገው ይገባል፡፡ አገርን የመስዋዕት በግ ለማድረግ የሚደረግን የሽብር እንቅስቃሴ ሁሉ “በቃ” ማለት የሚገባን ወቅት ላይ መሆናችንን ተገንዝበን ለአገር ሰላም መጠበቅ እና ሉዓላዊነት መከበር በጋራ እንቁም፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም