የህዝቡን ፍላጎት መሰረትአድርገው የተገነቡ ፕሮጀክቶች የልማት እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ያቃልላሉ-ከንቲባ ከድር ጁሃር

143

ድሬዳዋ፤ ሐምሌ 16/2014 (ኢዜአ)፡ የህዝቡን ፍላጎት መሰረትአድርገው የተገነቡ ፕሮጀክቶች  የልማት እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እንደሚያቃልሉ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃርተናገሩ ።

በድሬዳዋ አስተዳደር ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ የተገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች እየተመረቁ ነው።

ፕሮጀክቶቹን የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፈትያ አደም ፣የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር፣ የድሬዳዋ የብልፅግና ጽህፈት ቤት አመራሮችና የካቢኔ አባላት ፕሮጀክቶችን እየመረቁ ነው።

የድሬዳዋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የማስፋፊያ ህንፃዎች ፣ለችግር የተጋለጡ  የህፃናት ማሳደጊያና ሴቶች ማቆያ ማዕከላት፣ድልድዮች ፣የትምህርት ቤቶች ማስፋፋት ፕሮጀክቶች እየተመረቁ ካሉ ፕሮጀክቶች መካከል ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው።

በተጨማሪም የጤና ተቋማት፣የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣  ለወጣቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ እና የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን የሚያነቃቁ ሼዶችም የምርቃቱ አካል ናቸው።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በምረቃው ስነስርአት ላይ እንደተናገሩት የህዝቡን ፍላጎት መሰረትአድርገው የተገነቡት ፕሮጀክቶች  የልማት እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ያቃልላሉ ።

የድሬዳዋ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሱልጣን አሊይ በበኩላቸው እየተመረቁ የሚገኙት ፕሮጀክቶች በፍጥነት ወደ አገልግሎት ሲገቡ የህዝብን የማህበራዊና የምጣኔ ሃብት ጥያቄዎች የሚፈቱ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

ፕሮጀክቶቹ የስራ አጥነት ችግሮችን በማቃለል በኩልም የራሳቸው አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው አስረድተዋል።

ዛሬ በከተማው እየተመረቁ ከሚገኙት ፕሮጀክቶች በተጨማሪ በነገው ዕለትም የገጠሩን ህብረተሰብ የምግብ ዋስትና የሚያረጋግጡ የመስኖ እና የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች እንደሚመረቁ ጠቁመዋል።

እየተካሄደ በሚገኘው የምረቃ ሥነ-ሥርዓት የኃይማኖት አባቶች፣የሀገር ሽማግሌዎች ፣ዑጋዞች፣አባገዳዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም