በአረንጓዴ ልማት አሻራ ህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደረግ የሃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ

131

ሐምሌ 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአገሪቱ እየተከናወነ ባለው የአረንጓዴ ልማት አሻራና ሌሎች የልማት ስራዎች ህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደረግ የሃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ።

የአዲስ አበባ የሃማኖት ተቋማት ጉባዔ ከኢትዮጵያ የመጽሐፍ ቅዱስ ማህበርና ከአዲስ አበባ ከተማ የሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ጋር በመተባበር በጉለሌ ዕጽዋት ማዕከል “የአረንጓዴ አሻራ የአንድነትና የአብሮነት ማሳያ” በሚል መሪ ሃሳብ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር አካሂደዋል፡፡

የአዲስ አበባ እና የጉራጌ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የአዲስ አበባ ከተማ የሃማኖት ተቋማት ጉባዔ የቦርድ ሰብሳቢ ብጹዕ አቡነ መልከጼዲቅ፤ ህብረተሰቡ በአገሪቱ በሚከናወኑ የልማት ስራዎች ላይ በመሳተፍ የራሳቸውን አሻራ ሊያኖሩ ይገባል ብለዋል።

በትብብርና በቅንነት አገርን ለማልማት የሚሰራ ስራ ፈጣሪ የሚወደው በጎ ተግባር ስለመሆኑም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በአገረቱ እየተከናወነ ያለው የችግኝ ተከላ ህብረተቡ በመተባበር ሊተገብረው እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ዋና አላማ ሁሉም የየራሱን ሃይማኖት ጠብቆ፤ አንዱ የሌላውን አክብሮ በጋራ ጉዳዮች ላይ ደግሞ አብሮ መስራት ነው ብለዋል፡፡

በዛሬው ዕለት የተከናወነው ችግኝ ተከላ መረሃ -ግብርም በአገሪቱ ልማትና እድገት ላይ በትብበር ለመስራት ያለንን እውነታ ለማመላከትና ህብረተሰቡን ለማስተማር መሆኑን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ የሃማኖት ተቋማት ጉባዔ ምክትል ሰብሳቢ ሼህ ሱልጣን አማን፤ “ምድር የተፈጠረችው ከሰማይ ዝናብ ከምድር ደግሞ ቡቃያ እንዲበቅል ነው” ተብሎ በፈጣሪ መታዘዙን  አንስተዋል፡፡

በዛሬው ዕለት የተከናወነው የችግኝ ተከላም ይህንን የሚያመላክት ነው ብለዋል።

የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ የአካባቢን ሰለም በማስጠበቅና አረንጓዴ አሻራ ላይ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን አንስተዋል፡፡

የዛሬው መርሃ ግብርም የአንድነትና አብሮነት ማጠናከሪያ መድረክ እንዲሁም የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ አንዱ አካል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ከልማትና ከጸጥታ ስራ ባሻገር የአቅመ ደካማ ዜጎችን መኖሪያ ቤት ማደስ እና ሌሎች በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ተመልክቷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ቀነዓ ያደታ፤ የአረንጓዴ አሻራ ፕሮጀክት የተፈጥሮ ሚዛንን ለመጠበቅ ትልቅ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ ያለምንም ልዩነት ሁሉም በልማቱ ሊሳተፍ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም