ዩክሬን የእህል ምርት ከጥቁር ባህር ወደቦች ወደ ዓለም ገበያ እንድትልክ የሚያስችል ስምምነት ሩሲያና ዩክሬን ተፈራረሙ

495

ሐምሌ 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) የዩክሬን የእህል ምርት ከጥቁር ባህር ወደቦች ወደ ዓለም ገበያ እንዲወጣ የሚያስችል ስምምነት ሩሲያና ዩክሬን ተፈራርመዋል።

ትናንት በተርኪ ኢስታንቡል ዶሎምባቼ ቤተ-መንግስት የተደረገው የአገራቱ ስምምነት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) እና በተርኪ አደራዳሪነት የተፈጸመ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።

በኢንታንቡል በሚገኘው ዶሎምባቼ ቤተ-መንግስት በተደረገው ስምምነት ላይ የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እና የተርኪ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ታይብ ኤርዶጋን ተገኝተዋል።

በስምምነቱ አማካኝነት ዩክሬን በጦርነቱ ምክንያት ተዘግተው ከነበሩት የጥቁር ባህር ወደቦች የእህል ምርቶቿን ወደ ዓለም መላክ ያስችላታል።

ለአምስት ወራት በዘለቀው የዩክሬንና ሩሲያ ጦርነት 20 ሚሊዮን ቶን የሚጠጋ የዩክሬን ምርት ተከማችቶ መቀመጡ ተገልጿል።

በዚህም ምክንያት በዓለም ገበያ የምግብ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምርና የምግብ አቅርቦት እጥረት ተከስቷል።ስምምነቱ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ተግባራዊ መሆን እንደሚጀም የሮይተርስ ዘገባ ያመለክታል።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት ስምምነቱ ለአፍሪካ መልካም የሚባል ዜና ነው ብለዋል።

ሕብረቱ ሩሲያና ዩክሬን ለጦርነቱ ፖለቲካዊ መፍትሔ በመፈለግ መቋጫ እንንዲሰጡት እንደሚፈልግና ለዚህ አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም