በጎንደር ከተማ ከሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል

137

ሐምሌ 15 ቀን 2014(ኢዜአ) በጎንደር ከተማ ከሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን የከተማው ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ፡፡

የመምሪያው ሃላፊ አቶ ቻላቸው ዳኛቸው ለኢዜአ እንደገለጹት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የሀገር ውስጥ ቱሪስት ፍሰቱ በእጅጉ ጨምሯል።

በውጪ ሀገር ቱሪስቶች ላይ ተወስኖ የቆየው የከተማው የቱሪዝም ዘርፍ በኮቪድና በሰላም እጦት ምክንያት ተቀዛቅዞ መቆየቱን አስታውሰው፤በተጠናቀቀው በጀት አመት የሀገር ውስጥ ቱሪዝሙን ለማሳደግ በተደረገው ጥረት ውጤት መገኘቱን አስታውቀዋል።

በተለይም የገና እና የጥምቀት በዓላት ለቱሪዝሙ መነቃቃት አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል፡፡

”በተጨማሪም የአጼ ቴዎድሮስ ቁንዳላ ወደ ጎንደር ከተማ መጥቶ ለህዝብ እይታ ክፍት እንዲሆን መደረጉና የከተማውን የቱሪዝም ሀብትና ጸጋዎች ለማስተዋወቅ የተደረገው ጥረት ሀገር ውስጥ የቱሪዝም ፍሰቱን አሳድጎታል” ብለዋል፡፡

በ2013 በጀት ዓመት የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ቁጥር 57 ሺህ እንደነበር አስታውሰው፤ በ2014 በጀት አመት ይህ ቁጥር ወደ 325 ሺህ ማደጉን ተናግረዋል፡፡

ከሀገር ውስጥ የቱሪዝም ዘርፉም ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን አመልክተው፤ ይሄም በከተማው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መነቃቃት ላይ አስተዋጽኦ ማበርከት መቻሉን አስረድተዋል፡፡

በአዲሱ በጀት አመት ለሀገር ውስጥ ቱሪዝም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አመልክተው፤ የጎብኝዎችን ቁጥርም ወደ 700 ሺ ለማድረስ እቅድ ተነድፎ ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል፡፡

የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን ቁጥር ለማሳደግም በትምህርት ቤቶችና በመንግስታዊ ተቋማት የሀገርህን እወቅ ክበባት የሚጠናከሩበትና በአዲስ መልክ የሚደራጁበትን አቅጣጫ በማስቀመጥ ወደ ስራ መገባቱን አስረድተዋል።

”በውጪ ሀገር ቱሪስቶች ላይ የተንጠለጠለውን የከተማውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ በሀገር ውስጥ ቱሪዝም ስትራተጂ ሊቃኝ ይገባል” ያሉት ደግሞ የጎንደር አለም አቀፍ ቅርስ አስተዳዳሪ አቶ ጌታሁን ስዩም ናቸው፡፡

በጎንደር የአጼ ፋሲል አብያተ መንግስታትን ጨምሮ በአለም ቅርስነት የተመዘገቡ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ በርካታ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ቅርሶች መኖራቸውን አመልክተዋል፡፡

ለሀገር ውስጥ ቱሪዝም ፍሰቱ ማደግ ሀገር በቀል ማህበራትንና ክበባትን ማጠናከር አስፈላጊ ነው ያሉት አስተዳዳሪው በበጀት አመቱ የአጼ ፋሲል ቤተ መንግስትን የጎበኙ የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጎንደር ከተማ የግል አስጎቢኚዎች ማህበር ሊቀ-መንበር አቶ ፈንታሁን ያለው በበኩላቸው የኮቪድ ወረርሺኝ በቱሪዝም ፍሰቱ ላይ ባሳደረው ተጽእኖ ተጎጂዎች ሆነው መቆየታቸውን ጠቁመው፤ ”አሁን ላይ ግን የሀገር ውስጥ ቱሪዝሙ መነቃቃቱ ተስፋ ሰጥቶናል” ብለዋል።

የአጼ ፋሲል ቤተ-መንግስት ለመጎብኘት የመጣው የደሴ ከተማ ነዋሪ አቶ ሃብታሙ ምስጋናው ”የቱሪዝም ዘርፉን በዛለቂነት ለመሳደግ የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ማበረታታትና መደገፍ ይገባል” ብለዋል።

የሀገር ውስጥ ቱሪዝም የህዝቦችን ታሪክ፣ ባህል፣ እምነትና ሃይማኖት ለማወቅና ለመረዳት እንዲሁም አንድነትን ለማጠናከር የሚያስችል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ጠቁሟል፡፡

በጎንደር ከተማ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የአጼ ፋሲል ቤተ-መንግስትን ጨምሮ የደብረ ብርሃን ሥላሴ፣ የቁስቋም ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናትና ሌሎች ቅርሶች እንዳሉ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም