የመንገድ ልማት ዘርፍ የሚመራበት አገር አቀፍ ፖሊሲ እየተዘጋጀ ነው

162

ሐምሌ 15/2014 (ኢዜአ)፡ የመንገድ ልማት ዘርፍ የሚመራበት አገር አቀፍ ፖሊሲ እየተዘጋጀ መሆኑን የከተማ ልማትና መሰረተ-ልማት ሚኒስቴር ገለጸ።

በኢትዮጵያ የመንገድ ዘርፍ ረቂቅ ፖሊሲና አዋጅ ላይ ከተለያዩ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የከተማና መሰረተ-ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ፤ በአጠቃላይ የመንገድ ዘርፍ የሚመራበትን ግልጽ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ ረቂቅ ፖሊሲ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።

ለረቂቅ ፖሊሲው በቂ ግብአት በማግኘት ለማዳበር ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ማድረግ   መድረኩ አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል።

የመንገድ ዘርፍ ፖሊሲና አዋጅ ባለመኖሩ ዘርፈ-ብዙ ችግሮች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ፖሊሲው ከመንገድ ዘርፍ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን በዘላቂነት የሚፈታ መሆኑን አብራርተዋል።

ለመንገድ ልማት ጥያቄ  ምላሽ ለመስጠት፣ ለጋራ ሃብት አጠቃቀም፣ የአገር ውስጥ ሥራ ተቋራጮችና አማካሪዎችን አቅም ለማሳደግ፣ የወሰን ማስከበር ችግሮችን ለማስወገድ፣ የግብዓትና ሌሎችንም ችግሮች ለመፍታት ያግዛል ብለዋል።

ለፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት፣ ለመንገድ ቁጥጥር፣ አስተዳደርና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች በፖሊሲው ምላሽ የሚያገኙ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአገሪቱ የመንገድ አውታር በ1989 ዓ.ም ከነበረበት 26 ሺህ 500 ኪሎ ሜትር አሁን ላይ ከ160 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ መድረሱን ጠቁመዋል።

ለመንገድ መሰረተ-ልማት ግንባታ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አስታውሰው፤ በቀጣይም ብዙ ለመሥራት መዘጋጀት ይገባል ነው ያሉት ሚኒስትሯ።

የመንገድ ፖሊሲና አዋጅ፣ የመንገድ መሰረተ-ልማትን በተቀናጀና በተናበበ መልኩ ለማከናወን ስትራቴጂካዊ አቅጣጫ የሚያሳይ ፖሊሲና አዋጅ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

በመድረኩ ላይ የተሳተፉት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ዘሃራ ዑመድ፤ ከፍትሃዊነትና እኩል ተጠቃሚነት ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የፖሊሲው መዘጋጀት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋዬ ዳባ፤ ፖሊሲው ከወሰን ማስከበር፣ ከአካባቢ እና ሕብረተሰብ እንክብካቤና ጥበቃ፣ ከምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግርና ከሌሎች ጋር ተያይዞ ያሉትን አቅጣጫዎች ያመላክታል ብለዋል።

በፌደራልና በክልሎች መካከል የሥራ መደበላለቅ ሳይኖር ግልጽ ኃላፊነት በመስጠት መሥራት እንደሚያሰፈልግም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ፤ መንገዶችን በጥራትና በብዛት ለመሥራት የሁሉም ጥረት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የሕብረተሰቡ የመንገድ ጥያቄ፣ የተሰራውን መንገድ በአግባቡ ያለመጠበቅ፣ ዘርፉ ውስብስብ ችግሮች ያለበት በመሆኑ በርካታ መንገዶች ለመሥራት ክልሎችም ሊሳተፉ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም