በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከዳያስፖራው ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወደ አገር ቤት ተልኳል

179

ሐምሌ 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) በ2014 በጀት ዓመት ከዳያስፖራው 4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ወደ አገር ቤት መላኩን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር መሃመድ ኢድሪስ፤ በ2014 በጀት ዓመት የዳያስፖራው ተሳትፎ በሁሉም ዘርፎች ከፍተኛ እድገት የታየበት መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ያለፈችባቸው የተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ዳያስፖራው በአገሩ ጉዳይ ያለው ተሳትፎ እንዲጨምር ዋነኛ ምክንያት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በኢንቨስትመንት፣ በንግድ፣ በአገራዊ ጉዳዮችና በፕሮጀክቶች ክንውን ላይ ዳያስፖራው ከቀደሙት ዓመታት በተሻለ ተንቀሳቅሷል ሲሉ ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ ከዳያስፖራው 4 ቢሊዮን ዶላር (ሪሚታንስ) ይገኛል ተብሎ ታቅዶ 4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ማሳካት ተችሏል ብለዋል።

አገራዊ ፕሮጀክቶችንና የተጎዱ አካባቢዎችን ከመደገፍ አኳያ በዳያስፖራው ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉንም ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ ከ1 ሺህ በላይ የዳያስፖራ አባላት በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሳተፉ ለማድረግ ታቅዶ ከ1 ሺህ 800 በላይ በሂደት ላይ እንደሆኑ ጨምረዋል።

በፐብሊክ ዲፕሎማሲ በተለያዩ የዓለም አገሮች በሚሊየን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን የአገራቸውን ነባራዊ ሁኔታ በማሳወቅ ላቅ ያለ የዲፕሎማት ሚና የተወጡበት ዓመት እንደነበርም አስታውሰዋል።

በታላቁ የአገር ቤት ጥሪ ዳያስፖራው ከአገሩ ጎን በመቆም ያሳየው ድጋፍም ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም ከአገር የገጽታ ግንባታ ባለፈ በኢንቨስትመንት፣ በንግድና ቱሪዝም እንዲሁም ሌሎች አገራዊ ጥሪዎች የተሻለ ተሳትፎ እንዲደረግ ይሰራል ሲሉ አረጋግጠዋል።

በተለያዩ የዓለም አገራት የሚኖሩ ዳያስፖራዎች ኢትዮጵያን በተለያዩ ነገሮች በመደገፍ ያሳዩትን ተሳትፎ እንዲያጠናክሩም ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም