በዞኑ በበጋ ወራት በተከለሉ ተፋሰሶች ውስጥ የሚተከሉ ከ22 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መዘጋጀታቸው ተገለጸ

140
ጎንደር ግንቦት 10/2010 በማዕከላዊ ጎንደር በዘንድሮ የበጋ ወራት ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ በተከለሉ ተፋሰሶች ውስጥ  የሚተከሉ ከ22 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መዘጋጀታቸው ተገለጸ፡፡ የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ጀመረ ለኢዜአ እንደተናገሩት የችግኝ ተከላው የሚካሄደው በዞኑ 13 ወረዳዎች በህዝቡ ተሳትፎ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራ በተከናወነባቸው 500 ተፋሰሶች ውስጥ ነው፡፡ ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ በተከለሉ ቦታዎች የሚከናወነው የችግኝ ተከላ ስራ 23 ሺህ ሄከታር የሚሸፍን ሲሆን የተራቆቱ ተፋሰሶችና ገላጣ መሬቶች በስነ-ህይወታዊ ዘዴ እንዲጠናከሩ ይደረጋል፡፡ የችግኝ ተከላ ስራው ከቀጣዩ  ወር ጀምሮ እንደሚካሄድ ያመለከቱት ኃላፊው  በጉድጓድ ቁፋሮና ተከላ ስራውም ከ300ሺህ በላይ በልማት ቡድኖች የተደራጁ አርሶአደሮች እንደሚሳተፉ የሚጠበቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የሚተከሉ ችግኞቹን ዘላቂ በሆነ አግባብ ለመጠበቅና ለመንከባከብ እንዲቻልም ከወረዳ እስከ ቀበሌ  የዘለቀ አደረጃጀቶችን በመፍጠር አርሶአደሩ በኃላፊነትና በተጠያቂነት ተረክቦ የሚጠብቅበት ስርዓት መዘርጋቱን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም እያንዳንዱ ቀበሌ ከአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት ችግኞችን ሆን ብለው የቤት እንስሳት በማሰማራት ጉዳት የሚያደርሱ ግለሰቦችን የሚቀጡበት ማህበራዊ ደንቦች እንዲያዘጋጁ መደረጉን አመልክተዋል፡፡ በወገራ ወረዳ የብራ ቀበሌ አርሶአደር አየልኝ ሰጤ "የተፈጥሮ ሀብት ስራው በአካባቢያችን በግብርና ምርታማነት ላይ ያሳየውን ለውጥ በመገንዘባችን ጐትጓች ሳንፈልግ ተፋሰሶችን የመጠበቅና የማልማት ስራ በማከናወን ላይ እንገኛለን "ብለዋል፡፡ የአንድ ለአምስት የልማት ቡድን አደረጃጀትን በመጠቀም በክረምቱ ወራት ችግኝ ለመትከል መዘጋጀታቸውን የገለጹት ደግሞ በኪንፋዝ በገላ ወረዳ የጨጨሆ ቀበሌ አርሶአደር ወንድሙ ዋሴ ናቸው፡፡ አካባቢያቸው ዝናብ አጠርና የድርቅ ተጋላጭ በመሆኑ ባለፉት ዓመታት ለተፈጥሮ ሀብት ስራ የተለየ ትኩረት በመስጠት በእርከንና ክትሮች ላይ ችግኞችን በመትከል ሲንከባከቡ መቆየታቸውንም ተናግረዋል፡፡ በጎንደር ዙሪያ ወረዳ የጭንጫዬ ቀበሌ አርሶአደር ማሩ ቢያድግልኝ በበኩላቸው  ባለፉት ዓመታት በርካታ ችግኞች ቢተክሉም  ተንከባክቦ የመጠበቅ ልምድ እንደሚጎድላቸው ገልጸዋል፡፡ "ተፋሰሶች ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ተጠብቀው በማገገማቸው ለመስኖ ስራ የምናውለው በቂ ውሃ አግኝተናል " ያሉት  አርሶአደሩ የዛፍ ችግኞች የአፈር መከላትን ለማስቀረት ስለሚረዱ ትኩረት ሰጥተው እንደሚንከባከቡም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም