የመረጃና ደኅንነት ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ጀማሪ ባለሞያዎች አስመረቀ

96

ሐምሌ 14 ቀን 2014 (ኢዜአ)በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሥር የሚገኘው የመረጃና ደኅንነት ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በዛሬው ዕለት የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ጀማሪ ባለሞያዎች አስመርቋል፡፡

በመርሐግብሩ ላይ የተገኙት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ኮሚሽነር እንዳሻው ጣሰው ተመራቂዎች ህብረተሰቡን በቅንነት፣በትህትናና በታማኝነት ለማገልገል ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የኢሚግሬሽንና ተያያዥ ሥራዎች በባህሪያቸው ቅንነትን፣ዝቅ ብሎ ማገልገልንና ትህትናን ይጠይቃል ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ተመራቂዎች ጠንክረው በመሥራት ተቋማቸውንና ሀገራቸውን ለማሳደግ መጣር ይኖርባችዋል ብለዋል።

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ብሩህተስፋ ሙሉጌታ በበኩላቸው፤ዜጎች የሚገባቸውን አገልግሎት በበቂ ሁኔታ፣ ጥራትና ፍጥነት የማግኘት መብታቸውን ለማረጋገጥ ተመራቂዎቹ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል፡፡

ሁሉም ባለሙያዎች ሀገራዊ ጥቅሞችንና ደኅንነትን ባስጠበቀና ስነ ምግባር በተሞላበት ሁኔታ ማገልገል አለባቸው።

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አሁን የጀመረው የሰው ኃይል ሥልጠና የሪፎርሙ ትግበራ አካል በመሆኑ ቀጣይ አገልግሎቱ ለህብረተሰቡ ጥራትና ተዓማኒነት ያለው ቀልጣፋ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የጀመረውን የሰው ኃይል አቅም ግንባታ ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ብሩህተስፋ ተናግረዋል።

የብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ፕሬዚዳንት አቶ ወንድወሰን ካሳ በበኩላቸው፤ዩኒቨርስቲ ኮሌጁ ለኢሚግሬሽን ጀማሪ ኦፊሰሮች የሥራ ስምሪት የሚሆን ጠቃሚና ውጤታማ የሆኑ ሥልጠናዎችን ሠጥቷል ብለዋል።

ዩኒቨርስቲ ኮሌጁ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትን የሰው ሃይል አቅም በትምህርትና በሥልጠና እየገነባ እንደሚገኝ የጠቆሙትም አቶ ወንድ ወሰን፤ ለሃገር ውስጥ ባለድርሻ አካላትና ለውጭ አቻ የመረጃና ደኅንነት ተቋማትም የመረጃ ኪነ ሙያ ሥልጠና እየሠጠ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

ዩኒቨርስቲ ኮሌጁ ቀደም ሲል አጫጭር ሥልጠናዎች እንዲሁም በዲፕሎማና በዲግሪ ደረጃ ትምህርት ይሰጥ እንደነበረ የጠቀሱት አቶ ወንድወሰን፤ አቅሙን ከጊዜው ወደ ጊዜ በማሳደግ በ2015 ዓ.ም በኢንተለጀንስ ፣ በደኅንነትና በሳይበር ሴኩሪቲ የጥናት ዘርፎች በማስተርስ ዲግሪ መርሃ ግብሮች ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማሠልጠን ቅድመ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልጸዋል።

በቅርቡ የፀደቀው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የተሻሻለ የማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1276/2014 የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ተጠሪነት ለብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እንደሆነ መደንገጉ ይታወሳል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም