በአንድ እጃችን ችግኞችን እየተከልን በሌላ እጃችን ደግሞ ችግሮችን እየነቀልን ኢትዮጵያን የመገንባቱን ሥራ አጠናክረን እንቀጥላለን

75

ሀምሌ14/2014/ኢዜአ/ "በአንድ እጃችን ችግኞችን እየተከልን በሌላ እጃችን ደግሞ ችግሮችን እየነቀልን ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር የጀመርነውን ሥራ አጠናክረን እንቀጥላለን "ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህን ጨምሮ የፓርቲው ዋና ጽህፈት ቤት አመራሮችና ሠራተኞች በጉለሌ እጽዋት ማዕከል ችግኝ ተክለዋል።

አቶ አደም ፋራህ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ፓርቲያቸው ትናንት እና ዛሬ ላይ ያልተቸከለ ይልቅኑም የነገ ትውልድ ላይ የሚሰራ በመሆኑ ከያዛቸው ስትራቴጂዎች መካከል ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ መገንባት አንዱ ነው።

ከስትራቴጂው አካል የሆነው አረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ መቋቋም፣ የምግብ ዋስትና  ማረጋገጥ፣ የሥራ እድል ፈጠራን ማሳደግ፣ የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል ትልቅ ሚና አለው ብለዋል።

ብልጽግና ፓርቲ እንደ ገዥ ፓርቲ መርሃ-ግብሩ እንዲሳካ ከመምራት ባሻገር ከ12 ሚሊየን በላይ አባላት ያሉት በመሆኑ በየደረጃው ያሉ አመራርና አባላት ለሌላው ምሳሌ በመሆን በመርሃ-ግብሩ ላይ ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሲቪክ ማህበራት ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር አለሙ ስሜ ብልጽግና ፓርቲ በየጊዜው በሚፈጠሩ ውስብስብ ችግሮች ሳይንበረከክ ለመፍትሔው እየሰራ ያለ ፓርቲ ነው ብለዋል።

May be an image of 2 people and outdoors

ለነገው ትውልድ የተሻለች አገር ለማስረከብ አንዱ ማሳያ ችግኝ መትከል መሆኑን ገልጸው፤ "በአንድ እጃችን ችግኞችን እየተከልን በሌላ እጃችን ደግሞ ችግሮችን የመንቀል መርህ በመከተል ሰላምን በማረጋገጥና ሌሎች ማኅበራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ እየሰራን ነው" ብለዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያ ችግሮችን በትብብር ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ ብሔራዊ ምክክርና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ሁሉንም በየፊናቸው ለማስኬድ እየሰራ ነው ብለዋል።

በተለይም የድህነትና ለሰላም መደፍረስ መንሰኤ የሆኑ ችግሮችን መንቀል ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ካሊድ አልዋን እና የፓርቲው ጽህፈት ቤት አመራር አቶ ነብዩ ስሁል መርሃ-ግብሩ ምልዓተ-ሕዝቡን ባሳተፈ አግባብ እየተካሄደ ነው ብለዋል።

ከ80 በመቶ በላይ ክፍለ-ኢኮኖሚውን ለያዘው ግብርና ዘርፍ ምርታማነት፣ የመሬት ለምነትን መጠበቅና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን መከላከል ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ብልጽግና ፓርቲ እያካሄደ ባለው ሪፎርም "ችግሮችን እየነቀለ ችግኞችን በመትከል፤ መጥፎውን በበጎ፤ ጥላቻና ጽንፈኝነትን በወንድማማችነትና አገራዊ አንድነት እየተካ ይቀጥላል" ነው ያሉት።

በአገር አቀፍ ደረጃ ያጋጠሙ ችግሮች በየደረጃው እየተቃለሉ እንዲሄዱ እንደ መንግሥት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ተስፋ ሰጭ ለውጦች እየተመዘገቡ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም መትከል ብቻም ሳይሆን እንደ ብልጽግና የተከሉትን የመንከባከብ እሴቶችን ገቢራዊ ይደረጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም