ለኦሮሚያ ክልል የትምህርት ጥራት መረጋገጥ በየዞኑ ሞዴል ትምህርት ቤቶች ይደራጃሉ...የኦሮሞ ልማት ማህበር

69
አዳማ መስከረም 4/2011 በአዲሱ የበጀት ዓመት በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅና ብቁ የሰው ሃይል ለማፍራት ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መድቦ ወደ ትግባራዊ እንቅስቃሴ መግባቱን የኦሮሚያ ልማት ማህበር/ኦልማ/ ገለጸ። የማህበሩ ለቀመንበር አቶ ደጀኔ ኢቲቻ ለኢዜአ እንደገለጹ ማህበሩ ባለፉት 20 ዓመታት የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋጡ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣በትምህርትና በጤና መስክ ሲሰራ ቆይቷል። ዘንድሮ ማህበሩ ከሌሎች ማህበራዊ ልማቶች በመውጣት በትምህርት መስክ ብቻ ለመስራት ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ይዞ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መግባቱን አመልክተዋል። የትምህርት ጥራት ለክልሉም ሆነ ለሀገሪቷ  ህዝብ ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጦች ውጤታማነትና ለዕድገት ቀጣይነት  ወሳኝ ሚና ያለው በመሆኑ ማህበሩ በዜጎች የአእምሮ ልማት ላይ ትኩረት ማድረጉን ገልጸዋል። በዚህም በየዞኑ ካሉት ትምህርት ቤቶች አንድ ሞዴል ትምህርት ቤት በመስፈርት በመምረጥ በአዳሪ ትምህርት ቤት ደረጃ ለማዋቀርና የተሟላ የመማር ማስተማር አገልግሎት እንዲሰጥ ይደረጋል ብለዋል። የተመረጡ ትምህርት ቤቶችን ብቃት ባላቸው ማምህራን፣በመማሪያ ቁሳቁስ፣በላቦራቶሪና ቤተ-ሙከራ የማደራጀት ሥራ ማህበሩ በሙሉ አቅሙ እንደሚያከናውን ገልጸዋል። “በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅና ብቁ የሰው ሃይል ለማፍራት ከሚደረገው ጥረት ባሻገር  ሳይንቲስቶችን በጥራትና በብዛት ለማፍራት ግብ አስቀምጠን እየሰራን እንገኛለን” ብለዋል። “ማህበሩ በአሁኑ ወቅት በአዳማና ጉደር በሚገኙ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ከ400 በላይ ተማሪዎችን እያስተማረ ይገኛል”ያሉት አቶ ደጀኔ በለገጣፎ ለገዳዲ በ400 ሚሊዮን ብር ሶስተኛ አደሪ ትምህርት ቤት እየገነባ መሆኑንም ተናግረዋል። እየተገነቡ ያሉ አዳሪ ትምህርት ቤቶች የክልሉን ዞኖችና ወረዳዎች በሚፈለገው መልኩ ተደራሽ ሰለማያደርጉ በ20 የክልሉ ዞኖችና በሁሉም የከተማ መስተዳደሮች ውስጥ አንዳንድ ሞዴል ትምህርት ቤት ለማደራጀትና ተደራሽነታችንን ለማሳደግ ያለመ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል። በተጠናቀቀው የበጀት መት የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከወሰዱት 400 ተማሪዎች ውስጥ 360 የሚሆኑት 4 ነጥብ ያመጡ ሲሆን 31 የሚሆኑት ደግሞ ከ3 ነጥብ 8 በላይ ውጤት ማምጣታቸውን ጠቅሰው በተመሳሳይ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ከወሰዱት ውስጥ ከ600 በላይ ዘጠኝ ተማሪዎች ማምጣታቸውን አመልክተዋል። “ይህ ውጤት ሊመጣ የቻለው በሁለቱም አዳሪ ትምህርት ቤቶች የሚሰጠው መማር ማስተማር ጥራትን መሰረት የዳረገ ከመሆኑም ባለፈ ሳይንቲስቶችና ተመራማሪዎችን በብዛትና በጥራት ለማፍራት ጭምር ነው” ብለዋል። “በቀጣይነትም በችሎታቸው ልዩ ተሰጥዎ ያላቸውን ተማሪዎች በጥራትና በጥንቃቄ የመምረጥና የማስተማር ሥራ በማከናወን ለተሻለ የሰው ሃይል ልማት እንሰራለን” ብለዋል። የኦሮሚያ ልማት ማህበር የቦርድ አባልና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ በበኩላቸው ማህበሩ የሰው ሃይል ልማት ላይ በሙሉ አቅም ለመስራት ትኩረት ማድረጉ በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የሚደረገውን ጥረት የሚያሳካ መሆኑን ገልጸዋል። “በክልሉ 20 ዞኖችና ሁሉም የከተማ መስተዳድሮች የኦልማ ሞዴል ትምህርት ቤቶች ለማደረጃት በማህበሩ እየተደረገ ላለው ጥረት ትምህርት ቢሮውና የክልሉ መንግስት ሙሉ ድጋፍና እገዛ ያደርጋሉ” ብለዋል። ቤተ-ሙከራዎችን፣የአይሲቲ ማእከል፣ላቦራቶሪዎች፣የመመሪያ ክፍሎችና ቁሳቁሶችን በበቂ ሁኔታ የማሟላት ሥራ ላይ በጋራ እንሰራለን ብለዋል። አዳሪ ትምህርት ቤቱ በመማሪያ ቁሳቁስ፣አይሲቲና ቤተ- ሙከራዎች የተደራጀ በመሆኑ ለትምህርት ጥራትም ሆነ ዘንድሮ ላስመዘገብነው ውጤት ጉልህ ሚና ነበረው ያለው ደግሞ በኦሮሚያ ልማት ማህበር የአዳማ አዳሪ ትመህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ኑስበር ዱጉማ ነው። በሚደረገው ድጋፍ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ እያደረገው መሆኑንም ወጣቱ ተናግሯል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም