በአዳማ ከተማ በሕገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ ከ46ሺህ በላይ የአሜሪካን ዶላርና የወርቅ ጌጣጌጦች ተያዙ

217

አዳማ ሀምሌ 12/2014 (ኢዜአ) በአዳማ ከተማ ከ46ሺህ በላይ የአሜሪካን ዶላርና የተለያዩ ይዘት ያላቸው የወርቅ ጌጣጌጦች በሕገወጥ መንገድ ሲዘዋወር መያዙን የከተማዋ ፖሊስ አስታወቀ።

የአዳማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግኑኝነት ባለሙያ ምክትል ኢንስፔክተር ወርቅነሽ ገልሜቻ ለኢዜአ እንደገለጹት ገንዘቡ ከአዲስ አበባ ወደ ድሬደዋ በሚጓዘው ንብረትነቱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሆነ ኮድ 3/81280 ኢ.ት የሰሌዳ ቁጥር በያዘችው ደብል ገቢና ተሽከርካሪ ውስጥ በተደረገ ፍተሻ መያዙን ገልጸዋል።

ፖሊስ ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ በከተማዋ ደምበላ ክፍለ ከተማ ኢሬቻ ቀበሌ ልዩ ቦታ ቢኤም በሚባል ስፍራ ትናንት ምሽት አራት ሰዓት ተኩል መያዙን ተናግረዋል።

በዚህም 46ሺህ 421 የአሜሪካን ዶላርና የተለያየ ይዘት ያላቸው የአንገት ሃብሎች፣የእጅ ብራስሌቶችና የጆሮ ጌጣጌጦች መሆኑን አመልክቷል።

ከውጭ ሀገር ገንዘብ በተጨማሪ የተያዙት ንብረቶች የአንገት፣የእጅ ብራስሌቶች ፣የጆሮና የጣትን ጨምሮ በቁጥር 16 የሆኑ የወርቅ ጌጣጌጦች ናቸው ብለዋል።

አሽከርካሪውን ጨምሮ እጅ ከፍንጅ የተያዙ ግለሰቦች ላይ በፖሊስ የምርመራ መዝገብ እየተጣራበቸው መሆኑንም ምክትል ኢንስፔክተር ወርቅነሽ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ