የኢትዮጵያ ወጣቶች ከኤፍሬም ህይወት በመማር የትናንት ችግራቸው ሳያቆማቸው ለተሻለ ለውጥ መትጋት ይኖርባቸዋል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

111

ሐምሌ 11/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ወጣቶች ከኤፍሬም ህይወት በመማር የትናንት ችግራቸው ሳያቆማቸው ለተሻለ ለውጥ መትጋት እንደሚገባቸው የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጥሪ አቀረቡ።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኮምፒውተር ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪ ለተመረቀው ኤፍሬም በለጠ ቤተሰቦች ካሳንቺስ አካባቢ ከተገነባው የሰው ተኮር የመኖርያ ቤት ህንፃ ውስጥ ባለሁለት መኝታ ቤት በስጦታ አበረክተዋል።

ከንቲባዋ  በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የወጣት ኤፍሬም በለጠ ወላጅ እናት ወይዘሮ ተዋበች ኮይሻ የበርካታ ታታሪ ኢትዮጵያዊያን እናቶች ምሳሌ ነች።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሩቁ ኤፍሬም በለጠ በርካቶች ያልደፈሩትን የእናቶች ሸክም በአደባባይ የመሰከረ ለእናቶችም የሚገባውን ክብር ያሳየ ጀግና ነው ብለዋል።

በርካታ ኢትዮጵያዊያን እናቶች በመሰል ውጣ ውረድ አልፈው ልጆቻቸውን በማስተማር ለቁም ነገር እንደሚያበቋቸውም አንስተዋል።

ኤፍሬም በለጠን ወላጆቹ በሚገባ አስተምረውታል ያሉት ከንቲባዋ፤ የእናቶችን ደግነትና የሚያልፉበትን የህይወት ውጣ ውረድ በአደባባይ በመመስከር ለበርካቶች አርአያ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲመጣ የሚሰሩ ወጣቶች መበራከት እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ ወጣቶች ከኤፍሬም ህይወት በመማር የትናንት ችግራቸው ሳያቆማቸው ለተሻለ ለውጥ መትጋት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

በርካታ ውጣ ውረድን አልፈው ልጆቻቸውን ለቁም ነገር ላበቁ እንደ ወጣት ኤፍሬም ወላጆች ማስታወሻ እንዲሆንም የመኖሪያ ቤት ስጦታ ማበርከታቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪ ወላጁ እናቱ የሆኑት ወይዘሮ ተዋበች ኮይሻም በቂርቆስ ክፍለ ከተማ አዲስ በተገነባው የምገባ ማዕከል ቋሚ እናትነት የስራ እድል እንዲያገኙ እንደሚደረግም አረጋግጠዋል።

ስጦታ የተበረከተላቸው የኤፍሬም በለጠ ወላጅ እናት ወይዘሮ ተዋበች ኮይሻ እና ወላጅ አባቱ አቶ በለጠ ምስጌም ከንቲባዋ ላበረከቱላቸው የመኖሪያ ቤት ስጦታ ምስጋና አቅርበዋል።

ወጣት ኤፍሬም መመረቂያ ገዋኑን ለእናቱ በማልበስና በጀርባው እንጨት በመሸከም እናቱ እርሱን ለማሳደግና አስተምራ ለማስመረቅ የከፈለችውን ትልቅ ዋጋ በአደባባይ አሳይቷል።

"ዛሬ አምሮብን፤ አጊጠንና ጥሩ ለብሰን ስንታይ ብርቱዎች ሆነን ሳይሆን ብርቱ የሆኑ እናቶች ስላሉን ነው" በማለት የእናቶችን ከፍ ያለ ዋጋ አሳይቷል።

እናቶች ልጆቻቸውን የሚያስተምሩት እንጨት እየተሸከሙ፣ ከችግር ጋር እየታገሉ መሆኑን ተናግሯል።

እናቶች ዝቅ ብለው ለልጆቻቸው ከፍታ ያለ እረፍት እንደሚሰሩ እናቱን አብነት አድርጎ መስክሯል።

እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊን ወላጆች ሁሉ ወላጆቹ ከባድ ዋጋን ከፍለው እንዳስተማሩት ይናገራል።

በተለይም ወላጅ እናቱ ሆኑት ወይዘሮ ተዋበች "እናቴ በባዶ እግሯ እየሄደች እንጨት ለቅማ በመሸጥ ከባድ ዋጋን ከፍላ እዚህ አድረሳኛለች" ይላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም