የመጅሊሱ ምርጫ አሳታፊና የህዝበ ሙስሊሙን አንድነት የሚያመላክት መሆኑ ተገለጸ

111

ሐምሌ 11 ቀን 2014(ኢዜአ) የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባኤና ስራ አስፈፃሚ ምርጫ አሳታፊና የህዝበ ሙስሊሙን አንድነት የሚያመላክት መሆኑን የምርጫው ታዛቢዎችና ተሳታፊዎች ገለጹ፡፡

የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ በበኩላቸው አንድነትን በማጎልበት የህዝበ ሙስሊሙን ጥያቄዎች በእኩልነት ለመፍታት እንደሚሰሩም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የተቋማት ለውጥና አንድነት 2ኛ ዙር ጉባኤ መጅሊሱን ለሶስት ዓመታት የሚመሩ 30 የጠቅላላ ጉባኤና 14 የስራ አስፈፃሚ አባላትን መርጧል፡፡

በጉባኤው ላይም የምክር ቤቱን ፕሬዘዳንት፣ ሁለት ምክትል ፕሬዘዳንቶችና ዋና ጸሀፊን ጨምሮ 14 አባላት ያሉት የስራ አስፈፃሚ አባላት ተመርጠዋል፡፡

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት የምርጫ ታዛቢዎችና ተሳታፊዎች እንዳሉት፤ ዛሬ የተደረገው የመጅሊስ ምርጫ ሂደት የመጀመሪያው ዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊነትን የተከተለ አካሄድ ነው፡፡

የመጅሊሱ ስራ አስፈጻሚና ጠቅላላ ጉባኤ አባላት “እኔ” ሳይሆን “አንተ ተመረጥ” በሚል ፍጹም ቅንነትና አንድነት የታየበት ነበር ብለዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ ምርጫው የሙስሊሞችን አንድነት ያሳየ ሁሉም ክልሎች የፌደራል መጅሊስ ተወካዮቻቸውን በራሳቸው መንገድ መርጠው ያቀረቡበት እንደነበርም ገልጸዋል፡፡

በህዝበ ሙስሊሙ ዘንድ የተዋጣለትና ፍትሃዊ ምርጫ እንደነበር የገለጹት አስተያየት ሰጭዎቹ፤ ለዚህ አስተዋጽኦ የጎላ አበርክቶ ለነበራቸው የመንግስት አካላትም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ተመራጮቹም ህዝበ ሙስሊሙን በእኩልነት በማገልገልና ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት በቅንነት በመስራት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ህዝበ ሙስሊሙም መጅሊሱ ሃላፊነቱን በሚገባ እንዲወጣ ከጎን ሆኖ ማገዝና መደገፍ እንዳለበት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ በበኩላቸው የእስልምና እምነት ተከታዮች አንድነታቸውን ጠብቀው ለአገር ሰላምና ልማት በጋራ እንዲቆሙ ጠይቀዋል፡፡

የተሰጣቸውን ታላቅ ሃላፊነት በስኬት መወጣት እንዲችሉ ህዝበ ሙስሊሙ ከጎናቸው ሆኖ በጸሎት እንዲያግዛቸውም ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም