በጂንካ ከተማ የተከተው የእሳት አደጋ በቁጥጥር ስር ዋለ

206

ሐምሌ 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) በጂንካ ከተማ አስተዳደር ዛሬ ከቀኑ 9:00 አከባቢ ተከስቶ የነበረውን የእሳት አደጋ መቆጣጠር መቻሉን ፖሊስ አስታወቀ።

የጂንካ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር እንዳወቀ መኩሪያ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በተከሰተው ድንገተኛ የእሳት አደጋ አምስት የንግድ ድርጅቶች ላይ ጉዳት ደርሷል።

የአደጋው መንስኤና ያስከተለው ጉዳት በመጣራት ላይ እንደሆነ ገልጸው፤ በአሁኑ ሰአት በአከባቢው በሚገኙ የጸጥታ ሃይሎች፣ በህብረተሰቡና በጂንካ የአየር ማረፊያ የእሳት ማጥፊያ ተሽከርካሪ የጋራ ርብርብ አደጋውን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር መቻሉን ተናግረዋል።

በአደጋው ጉዳት በደረሰባቸው ሱቆች ውስጥ ህገወጥ የቤንዚን ክምችት በመኖሩ አደጋውን የመቆጣጠር ስራ አዳጋች አድርጎት እንደነበር ኮማንደር እንዳወቀ ገልጸዋል።

በህገወጥ መንገድ ቤንዚን በቤት ውስጥም ሆነ በንግድ ተቋማት ውስጥ ማከማቸት ለከፍተኛ አደጋ የሚያጋልጥ መሆኑን በመገንዘብ በህገወጥ የቤንዚን ሽያጭ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም