ለውጡ የሲቪክ ማህበራት ማቋቋሚያ አዋጁን ለማሻሻል ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል

60
ባህርዳር መስከረም 4/2011 የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ዘመን ተሻጋሪ የሲቪክ ማህበራት ማቋቋሚያ አዋጅን ለማሻሻል ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት መድረክ አስታወቀ። መድረኩ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ተግባራዊ ተደርጎ የነበረውን አዋጅ ቁጥር 621/2001 ለማሻሻል የሚያስችል ረቂቅ በማቅረብ ግብዓት ለመሰብሰብ ያለመ አውደ ጥናት በባህርዳር ከተማ ዛሬ አካሂዷል። የመድረኩ አስተባበሪ አርቲስት ደሳለኝ ሃይሉ እንዳለው ባለፉት ዓመታት የተተገበረው አዋጅ ህዝቡ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱን ለማስከበር አደረጃጀት ፈጥሮ እንዳይንቀሳቀስ ገድቦታል። "በገንዘብ ማመንጨትና ግኝት፣ በተግባርና ዓላማ ስምሪት፣ በበጀት አጠቃቀምና ሌሎች ጉዳዮች አዋጁ አሰሪ እንዳልነበር ማሳያ ነው" ብሏል። ይህም ማህበራትና በጎ አድራጎት ድርጅቶች በሌሎች ዓለማት እንደሚታየው የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነትና ተግባር ከመወጣት ይልቅ እንዲከስሙ እንዳደረገ ገልጿል። መንግስት ግልጽነት የሰፈነበት አሰራር እንዲያሰፍን የሚጎተጉቱ አካላት በመክሰማቸውም ባለፉት ሶስት ዓመታት በሀገራችን የጎዳና ላይ ነውጥ፣ ሁከትና ብጥብጥ እንዲከሰት ምክንያት መሆኑን አስረድቷል። "በአሁኑ ወቅት የተቋቋመው መድረክም ዓለም አቀፍ መርሆዎች ላይ የተመሰረተ ዘመን ተሻጋሪ የበጎ አድራጎትና ማህበራት አዋጅ በማውጣት በኢትዮጵያ የሚካሄዱ ኢኮኖሚያዊ፣  ፖለቲካዊና ማህበራዊ ልማቶችን ለመደገፍ ያለመ ነው'' ብሏል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ የሆኑትና የመድረኩ አባል ዶክተር ታደሰ ካሴ በበኩላቸው እንደተናገሩት የተዘጋጀው ረቂቅ ከስሙ ጀምሮ የማያሰሩ አንቀጾችን አንድ በአንድ በመፈተሽ እንዲሻሻል የሚያደርግ ነው። "አስገዳጅ ምዝገባ፣ ቁጥጥር ላይ የተመሰረተ የመንግስት አሰራር፣ የገንዘብ ምንጭ፣ ዓላማና ተግባርን የሚወስኑ ድንጋጌዎችን ለማሻሻል በሚያስችል መልኩ በትኩረት የታዩ ናቸው" ብለዋል። በኢፌዴሪ ህገ-መንግስት አንቀጽ 31 መሰረትም ማንኛውም ዜጋ ሁለትና ከዚያ በላይ ሆኖ በመደራጀት ለህዝቡ መብት፣ ጥቅምና ለሀገር ልማት አስተዋጽኦ የሚያደርግበትን እድል እንደሚሰጥ አስረድተዋል። በመብትና ዴሞክራሲ ማስጠበቅ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችን በመወከል የመድረኩ አባል አቶ መሱድ ገበየሁ እንደገለጹት የነበረው አዋጅ በተለይም በሰብአዊ መብትና በዴሞክራሲ ላይ የተሰማሩ ማህበራትና ድርጅቶችን የጎዳ ነበር። "በአቅም ግንባታ፣ በስልጠና፣ በቁሳቁስ ድጋፍና የሌሎች አገራትን ተሞከሮ በማምጣት ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት መጎልበት ሲሰሩ የነበሩ አካላት ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ስራቸውን አቁመው ነበር" ብለዋል። አሁን ተቋቁሞ እየሰራ የሚገኘው የበጎ አድራጎትና ማህበራት መድረክ በአዋጅ ተደግፈው የተዘረጉ አሰራሮችን እንዲሻሻሉ በማድረግ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየመጣ ያለውን ለውጥ ዳር ለማድረስ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል። በግብዓት ማሰባሰቢያ ዓውደ ጥናቱ ላይም የዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ የሲቪልና የሙያ ማህበራት፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ የመንግስት አካላትና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም