በኢትዮጵያ ያለውን ከፍተኛ የእንፋሎት ኃይል በአግባቡ መጠቀም እንዳልተቻለ ተገለጸ

110
አዲስ አበባ  መስከረም 4/2011  በኢትዮጵያ ከእንፋሎት (የጂኦተርማል) የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የሚያስችል እምቅ አቅሟን በሚፈለገው መጠን ወደ ሃብት በመቀየር መጠቀም እንዳልቻለች ተገለጸ። የዓለም አቀፍ ልምዶችን በመቀመርና ተቋማዊ አቅምን በማሳደግ የእንፋሎት ኃይል ልማትን ማጎልበት እንደሚገባ የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር አሳስቧል። ሚኒስቴሩ ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር ከእንፋሎት ኃይል ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅምን ለማሳደግ ከሌሎች አገሮች ልምድ ለመቅሰም የሚያስችል የምክክር አውደ ጥናት ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ አካሂዷል። በዚሁ ወቅት ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ከእንፋሎት ኃይል ኤሌትሪክ ለማመንጨት እምቅ አቅም ቢኖራትም በፋይናንስና በሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ሳቢያ ከዘረፉ መጠቀም አልተቻለም፡፡ ኢትዮጵያ ከእንፋሎት ብቻ  ከ10 ሺ ሜጋዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳላት ጥናቶች ይጠቁማሉ። ይህም ሆኖ እስካሁን ከዘርፉ ማመንጨት የተቻለው የኤሌክትሪክ ኃይል ከሰባት ሜጋ ዋት አይበልጥም ተብሏል። ለዘረፉ እድገት ማነቆ የሆኑትን ተግዳሮቶች በመከላከል ዘረፉን በወጉ ማልማት እንዲቻል "ዓለም አቀፍ ልምዶችን መቀመርና ተቋማዊ አቅምን ማሳደግ ይገባል" ሲሉ ሚኒስትሩ ገልፀዋል። በተለይም ከዘርፉ ልማት ጋር በተያያዘ ያሉ ተቋማዊ አሰራሮችን፣ አዋጆችንና መመሪያዎችን የተመለከቱ አዋጭ ልምዶችን ተግባራዊ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል። ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በፊት በዘርፉ ልማት ዙሪያ ያወጣቻቸውን አዋጆችና ህጎች የመከለስ ተግባር የተጀመረ ሲሆን፤ ከዚህ አኳያ ይህ አውደ ጥናት  ጠቃሚ ግብዓት እንደሚሰበሰብበት ተናግረዋል። በአለም ባንክ 'የኢነርጂና ኤክስትራክሽን ግሎባል ፕራክቲስ' ዳይሬክተር ሚስተር ሉሲዮ ሞናሪ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ የእንፋሎት ኃይል ልማትን ለማምጣት እንዲቻላት ለረዥም ጊዜያት የቆዩ እንቅስቃሴዎችን እያከናወነች ትገኛለች። በመሆኑም "በአሁኑ ወቅት አገሪቷ ወደ ልማት ላስገባቻቸውና ለምታስገባቸው የእንፋሎት ኃይል ልማት ፕሮጀክቶች የአለም ባንክ ድጋፍ ያደርጋል" ብለዋል። ኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦትን ለማሳደግ በኢነርጂው መስክ እያደረገች ያለው የተለያዩ ማሻሻያዎች የሚበረታቱ እንደሆነ ተናግረው፤ አገሪቷ ጠንካራ ተቋምና የማስፈጸም አቅምን ለመገንባት ለጀመረችው ጥረትም ባንኩ ድጋፍ እንደሚያደርግ አክለዋል። በአውደ ጥናቱ ላይ ላይ የመወያያ ወረቀት ያቀረቡት ዶክተር ሰለሞን ከበደ በበኩላቸው፤ "በኢትዮጵያ ትልቅ የእንፋሎት ኃይል እምቅ አቅም ቢኖርም በሚፈለገው ደረጃ እያደገ አይደለም" ሲሉ ተናግረዋል። በዘርፉ ያሉ እድሎችንና ተግዳሮቶችን በማጥናት መንግስታዊ ተቋማትና ባለኃብቱ ለዘርፉ ልማት ተባብረው  የሚሰሩበት ምቹ ሁኔታን መፍጠር እንደሚገባ አሳስበዋል። የአውደ ጥናቱ ዓላማ ኢትዮጵያ ያላትን የእንፋሎት ኃብት በብቃት መጠቀም ትችል ዘንድ ከኬንያ፣ ከሜክሲኮና ከቱርክ በዘረፉ ያላቸውን አዎንታዊ ልምድ መቅሰም መሆኑ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም