አዴኃን የአማራን ህዝብ መብትና ጥቅም በሰላማዊ ትግል ለማስከበር ጠንክሮ እንደሚሰራ አስታወቀ

98
ባህርዳር መስከረም 4/2011 የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ /አዴኃን/ አሁን በሀገር ውስጥ የተፈጠረውን ሰላም በመጠቀም የአማራን ህዝብ መብትና ጥቅም በሰላማዊ ትግል ለማስከበር ጠንክሮ እንደሚሰራ አስታወቀ። ባለፈው እሁድ ባህርዳር ለገባው የአዴኃን አመራሮችና ታጋዮች የከተማው ህዝብ  ዛሬ  አቀባበል አድርጎላቸዋል። በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በተካሄደው የአቀባበል ስነስርዓት ወቅት የአዴኃን ሊቀመንበር ታጋይ ተፈሪ ካሳሁን  እንደተናገሩት ድርጅቱ ወደትጥቅ ትግል የዛሬ ስምንት ዓመት እንዲገባ ያስገደደው በአማራው ላይ ይፈፀም የነበረውን የአስተዳደር በደል በመቃወም ነው። ድርጅቱም በቅርቡ የቀረበለትን የሰላም ጥሪ በመቀበል በኤርትራ በረሃ ሲያካሂድ የቆየውን የትጥቅ ትግል አቁሞ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል በመወሰን ከኤርትራ ወደ ባህርዳር ከነሰራዊቱ ገብቷል። አማራ እንደሌሎች የብሄር ድርጅቶች ጠንካራ ድርጅት ባለመኖሩ ባለፉት 27 ዓመታት ህዝቡ በማንነቱ በደል ሲፈፀምበት መቆየቱን ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡ አዴኃን ተደራጅቶ ወደ ትጥቅ ትግል ሲገባም አማራ እራሱን ከጥቃት በመከላከል የሀገሩን፣  የራሱን መብትና ጥቅም እንዲያስጠብቅ ለማድረግ እንደሆነም ተናግረዋል። "በቀጣይም ድርጅቱ በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ተመዝግቦ ህጋዊ ሰውነት በማግኘት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችን በየአካባቢው ከፍቶ  የአማራና የኢትዮጵያን ህዝብ መብትና ጥቅም ለማስከበር  ይሰራል "ብለዋል። በተለይም ተመሳሳይ አቋም ከሚያራምዱ ከአማራ ድርጅቶች ጋር ወደፊት በመዋሃድም የአማራ ህዝብ የማንነት ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ ድርጅቱ የጀመረውን ትግል አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል። በአቀባበሉ ላይ የተገኙት የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙሉቀን አየሁ በበኩላቸው አሁን በሀገሪቱ የተፈጠረውን ሰላም ተከትሎ ለዴሞክራሲ መስፈን በስደት ሲታገሉ የቆዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደሃገራቸው እየገቡ መሆናቸውን ገልጸዋል። ከንቲባው እንዳሉት በሀገሪቱ በሚስተዋለው የመልካም አስተዳደር፣ በሰብአዊ መብት አያያዝና በፍትሃዊ ተጠቃሚነት ችግሮች ምክንያት ልጆቿ በስደት ተበታትነው እንዲኖሩ አድርጓል። "ለዓመታት ተበታትነው የቆዩ ልጆቿ ልዩነትን አጥብበው በዴሞክራሲያዊ ባህልና በመደማመጥ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል ሁላችንም በጋራ ልንሰራ ይገባል" ብለዋል። የከተማ አስተዳደሩም ከህዝቡ ጋር በመሆን ወደክልሉ  ለገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንድ በሚያደርጉ ጉዳዮች በጋራ ለመስራትና ለውጡን ለማቀጠል ዝግጁ እንደሆነም አረጋግጠዋል። የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ /አብን/ ሊቀመንበር ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ እንደገለጹት ባለፉት ዓመታት አማራ በጠላትነት ተፈርጆ ህዝቡ ለከፋ ስቃይና ሰቆቃ ተዳርጎ ቆይቷል። ሲፈፀምበት የቆየውን ግፍና መከራ ለማስቆም የአማራ ዴሞክራሲ ኃይል ንቅናቄ በኤርትራ በረሃ የትጥቅ ትግል ሲያካሂድ መቆየቱን ጠቅሰዋል። የአማራን ህዝብ መብትና ጥቅም በዘላቂነት ለማስከበርም በቀጣይ አንድ ጠንካራ ድርጅት በማቋቋም ህልውናውንና አንድነቱን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አመለክተዋል። በአቀባበሉ ስነስርዓት የባህርዳር  ህዝብ፣  የከተማዋ አስተዳደር ስራ ኃላፊዎችና ሌሎች እንግዶችም ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም