በአቶ አብዲ መሐመድ ኡመርና ሌሎች ተጠርጣሪዎች ላይ ፖሊስ የጠየቀው ጊዜ ቀጠሮ ተፈቀደ

1050

አዲስ አበባ   መስከረም 4/2011 በሱማሌ ክልል የቀድሞ ርዕሰ-መስተዳደር አብዲ መሐመድ ዑመርና በሌሎች ተጠርጣሪዎች ላይ ፖሊስ የጠየቀው የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ  ፍርድ ቤት ፈቀደ።

አቶ አብዲ መሐመድ ኡመርን ጨምሮ በክልሉ በተፈጠረ ግጭት ተጠርጥረው የተያዙ አራት ተጠርጣሪዎች ዛሬ በልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

ተጠርጣሪዎቹ አንደኛ ተከሳሽ አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር፣ ሁለተኛ ተከሳሽ ወይዘሮ ራህማ መሐመድ፣ ሶስተኛ ተከሳሽ አቶ አብዱራዛቅ ሰሀኒ እና አራተኛ ተከሳሽ ፈርሃን ጣሂር ሲሆኑ፤ ተጨማሪ ምርመራ እንዲካሄድባቸው ፖሊስ በጠየቀው መሰረት ፍርድ ቤቱ የምርመራ ጊዜውን ፈቅዷል።

 ፖሊስ ከዚህ ቀደም በፍርድ ቤቱ የተሰጠውን የጊዜ ቀጠሮ በመጠቀም 117 ምስክሮችን ቃል እንደተቀበለ፣ የሰነድ ማስረጃዎችን የመመርመርና የሞባይል ስልኮች ምርመራ ሲያካሂድ መቆየቱን ገልጾ ቀሪ ስራዎች ያሉት በመሆኑ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።

ቀሪ ምስክሮችን የመስማት፣ የተደበቁ የጦር መሳሪያዎች በመኖራቸውን ያንን የማጣራት፣ በክልሉ በደረሰው ጉዳት ጥቃት የተፈጸመባቸውን ሰዎች ማንነት የማጣራት፣ የቴክኒክ ምርመራ ውጤትን የመጠበቅ፣ እንዲሁም ‘ሂጎ’ በሚል ስያሜ የተደራጀ ቡድንን የማጣራት ተጨማሪ ስራዎች የሚቀሩት በመሆኑ የተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮውን ጠይቋል።

ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አቶ አብዲ መሐመድ ቤተሰባቸውን እንዳያገኙ መከልከላቸውን፣ የመናገር መብታቸው እንደታፈነ፣ በካቴና ታስረው እንደሚሰቃዩ፣ ማስፈራራት እንደሚደርስባቸው ካለባቸው ህመም ጋር የሚስማማ ምግብ እንደማያገኙና ቤተሰቦቻቸው ከቤት እንዲወጡ ተደርገዋል ሲሉ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታቸውን አሰምተዋል።

አቶ አብዱራዛቅ የተባሉት ተጠርጣሪ ከታሰሩ 19 ቀናት እንደሆናቸው በመግለጽ በጨለማ ቤት ታስረው እንደሚገኙና የታሰሩት በጥርጣሬ በመሆኑ የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ጠይቀዋል።

ወይዘሮ ራህማ መሐመድ በበኩላቸው የደም ግፊትና የአስም በሽተኛ ሆነው ሳለ መድሃኒት እንዳላገኙ ተናግረዋል።

የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች ደንበኞቻቸው የቀረበባቸው የተጠርጣሪነት ክስ ተነጣጥሎ እንዲቀርብና የዋስትና መብታቸው እንዲከበር  ጠይቀዋል።

ፖሊስ ለቀረበው የተጠርጣሪዎች አቤቱታ በሰጠው ምላሽ ተጠርጣሪዎቹ በክልሉ በነበራቸው ስልጣን ተቀናጅተው ‘ሄጎ’ የተባለውን ቡድን በማደራጀት ተጠርጣሪዎቹ ዘርና ቀለምን በመለየት ጉዳት በማድረስና አመጹን በበላይነት ሲመሩ የቆዩ በመሆናቸው የዋስትና መብታቸው እንዳይከበር ተከራክሯል።

ተጠርጣሪዎቹ መድሃኒት፣ ምግብና ውሃ በአግባቡ እየቀረበላቸው እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ ያስረዳው ፖሊስ ምንም አይነት የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳልደረሰባቸው አስረድቷል።

ባሉበት ሆነው አስፈላጊው ህክምና እያገኙ እንደሆነም አመልክቶ፤ የወንጀል ክስ ሲመሰረትም ተነጣጥሎ እንደሚካሄድ ጠቁሟል።

ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎቹ የምግብ፣ የውሃና የመድሃኒት ጥያቄያቸው በአግባቡ እንዲሟላ ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን፤ ቁርዓንን ጨምሮ መጽሐፍት እንዲፈቀድላቸውና ሰብዓዊ አያያዙ በትክክል እንዲተገበር ትዕዛዝ አስተላልፏል።

ተጠርጣሪዎቹ ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ አድርጓል።