"ሀገርን እና ትውልድን ለማሻገር የሙያ ሚና ሳይደበላለቅ ሁሉም በተሰማራበት ዘርፍ የሚጠበቅበትን ሀላፊነት መወጣት አለበት" ጋዜጠኞች

170

ሐምሌ 9/2014  (ኢዜአ )  ሀገርን እና ትውልድን ለማሻገር የሙያ ሚና ሳይደበላለቅ ሁሉም በተሰማራበት ዘርፍ የሚጠበቅበትን ሀላፊነት መወጣት አለበት ሲሉ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛ ዲግሪ የተመረቁ ጋዜጠኞች ገለፁ።

አንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በተለያዩ መርሓ ግብሮች ያስተማራቸውን ከ5 ሺህ በላይ ተማሪዎች  በዛሬው እለት አስመርቋል።

ኢዜአ ካነጋገራቸው ተመራቂ ተማሪዎች መካከል በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት በጋዜጠኝነት እያገለገሉ ያሉ ባለሙያዎች ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ባልደረባ ጋዜጠኛ ሰለሞን ሀይለየሱስ እና የኢቢኤስ ቴሌቭዥን ባልደረባዋ ጋዜጠኛ ናፍቆት ትዕግስቱ ሁሉም በተሰማራበት ሙያ ሀገርና ህዝብን የሚያሻግር ስራ የመስራት ሀላፊነት አለበት ብለዋል።

ጋዜጠኛ ሰለሞን ሀይለየሱስ፤ ሁሉም ሙያ የሚጠይቀውን እውቀትና ክህሎት መሰረት በማድረግ የሙያ መደበላለቅ ሳይኖር ለሃገር መስራት እንደሚገባ አንስቷል።

ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሙያ መደበላለቅ እየተስተዋለ እንደሚገኝ ገልፆ ለአብነትም ከሙያቸው ውጭ የፖለቲካ ተንታኝ የመሆን ዝንባሌ በበርካቶች ዘንድ እየታየ መምጣቱን ተናግሯል።

ይህ የሙያ መደበላለቅ ደግሞ በሀገር ሰላምና ደህንነት ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽእኖ የሚፈጥር በመሆኑ ሁሉም ሙያው ላይ በማትኮር የሚጠበቅበትን ሀላፊነት መወጣት አለበት ብሏል።

ጋዜጠኛ ናፍቆት ትዕግስቱ በበኩሏ በተሰማሩበት ሙያ ራስን የማብቃትና የማሳደግ ስራ በመስራት ሀገርን እና ህዝብን የሚያሻግር ተግባር ላይ ማተኮር እንደሚገባ ተናግራለች።።

በሙያዋ ለህዝብ የሚጠቅሙ መረጃዎችን በማድረስ ረገድ የሚጠበቅባትን ሀላፊነት ለመወጣት ያላትን ዝግጁነትም ገልጻለች።

በኢትዮጵያ ሰላም እንዲመጣ በሰከነ መንገድ መደማመጥ እና ተነጋግሮ መግባባት ይገባል የሚለው ጋዜጠኛ ሰለሞን ሀይለየሱስ ሁሉም ተናጋሪ ከሆነ ችግሮችን መፍታት አዳጋች እንደሚሆን ተናግሯል።

እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታትና ሀገርን ለማጽናት ህዝብና መንግስት መደማመጥ እንዳለባቸውም ጠቁሟል።

ሰላም ከሌለ በተሰማሩበት ሙያ ማገልገል እንደማይቻል የገለጸችው ጋዜጠኛ ናፍቆት ትዕግስቱ ከሁሉ በፊት የሀገር ሰላምና አንድነትን መጠበቅ ላይ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት ብላለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም