ምሩቃን ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የምርምር ስራዎች ላይ ሊያተኩሩ እንደሚገባ ተመለከተ

77

ሶዶ፣ ሀምሌ 9/2014(ኢዜአ) ምሩቃን በተማሩበት መስክ የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎች በዘላቂነት መመለስ የሚያስችሉ የምርምር ስራዎችን ማፍለቅ ላይ ሊተኩሩ እንደሚገባ ተመለከተ ።

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ከ4 ሺህ 400 በላይ ተማሪዎቹን ዛሬ አስመርቋል።

በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የአዲስ ኮንትኔንታል የጤና አጠባበቅ ዋና ዳይሬክተርና የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ፕሮፌሰር የማነ ብርሃን እንዳሉት  ተመራቂዎች የህብረተሰብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የምርምር ስራዎች ላይ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል።

በሀገሪቱ ለትምህርት የተሰጠውን ትኩረት እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማፋጠን መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በተለይ ተመራቂ ተማሪዎች አገራዊ አደራ ያለባቸው መሆኑን ገልፀው በሰለጠኑበት የሙያ መስክ የህብረተሰቡን ዘላቂ ጥቅምና የልማት ጥያቄን መመለስ የሚያስችሉ የምርምር ስራዎች የማከናወን ሃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በትምህርት ቆይታቸው የቀሰሙትን ዕውቀት በመጠቀም ወደ ማህበረሰቡ በሚቀላቀሉበት ወቅት በተጨባጭ ምላሽ ሊሰጡ የሚችሉ አገልግሎቶች በመስጠት ለሀገርና ለህዝብ እፎይታ ሊሆኑ እንደሚገባ ፕሮፌሰር የማነ አስገንዝበዋል።

ምሩቃን ሰላሟና ሉዓላዊነቷ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን ለመገንባት ጉልህ ድርሻ ያላቸው በመሆኑ ያላቸውን አቅም እንዲጠቀሙ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በርካታ ስራዎች እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ በምርምርና የማህበረሰብ  አገልግሎት በቴክኖሎጂ ለማስተሳሰር የሚያስችሉ ስራዎች በልዩ ትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ነው የጠቀሱት ።

የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመዋል።

የግብርና ዘርፉን ማዘመን፣ በጤና ተቋማት ተደራሽነትና የአገልግሎት ጥራት ማስጠበቅ ዩኒቨርሲቲው በትኩረት እያከናወናቸው ካሉ ተግባራት መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን አመልክተዋል ።

በዩኒቨርሲቲውና በአከባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ያለው ቁርኝት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው ለዩኒቨሲቲው የመማር ማስተማር ሰላማዊነት ወሳኝ ሚና እየተወጣ መሆኑን አመላክተዋል።

የዩኒቨርሲቲው ተመራቂ ተማሪዎች ወደ ማህበረሰቡ በሚቀላቀሉበት ወቅት ስራ ፈጣሪና ለማህበረሰቡ እፎይታ እንዲሆኑ ለማስቻል የህይወት ክህሎት ስልጠናዎች መስጠቱን አስታውቀዋል።

በዩኒቨርሲቲው ከኢንፎርሜሽን ሲስተም ትምህርት ክፍል 3 ነጥብ 9 በማምጣት  የዋንጫ ተሸላሚ ተመራቂ ሙሉቀን ጎዳቶ በእቅድ በመመራት ለውጤት መብቃቱን ተናግሯል።

በቀጣይ ወደ ስራ መስክ ሲቀላቀል ለማህበረሰቡ ጠቃሚ የሆኑ የምርምር ስራዎች ለመስራት ያለውን ዝግጁነት ገልጿል።

ሌላኛዋ ከኢንፌርሜሽን ቴክኖሎጂ ትምህርት ክፍል በ3 ነጥብ 7 በማምጣት የሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነችው ተመራቂ ሊሊ ገርማሞ ጊዜዋን በአግባቡና በዕቅድ መምራት መቻሏ ለስኬቷ  እንደረዳት ትናግራለች።

"በንድፈ ሀሳብና በተግባር የተማርኩትን ትምህርት በመጠቀም ወደማህበረሰቡ በምቀላቀልበት ወቅት  ውጤታማ ለመሆን እተጋለሁ" ስትል ገልፃለች።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የተሳተፉ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የተመራቂ ቤተሰቦችና ተመራቂዎች የችግኝ ተከላ ስነ ስርአት አካሂደዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም