ሰላማችንን እየጠበቅን ልማታችንን ለማፋጠን በርትተን እንሰራለን - አቶ ፀጋዬ ማሞ

115

ሚዛን አማን፣ ሐምሌ 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) ሰላማችንን እየጠበቅን የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የልማት ስራዎችን በርትተን እንሰራለን ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞ አስታወቁ። 

በክልሉ ቤንች ሸኮ ዞን ከ39 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የሸኮ ኮንስትራክሽን እና ኢንዱስሪያል ኮሌጅ ዛሬ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።

በሸኮ ወረዳ ተገኝተው ኮሌጁን በይፋ መርቀው የከፈቱት አቶ ጸጋዬ ማሞ "ሰላማችንን እየተጠበቅን ለህዝብ ተጠቃሚነት ፋይዳ ያላቸው የልማት ስራዎችን በትጋት እንሰራለን" ብለዋል።

"በየትኛውም አካባቢ ሰላም ካለ ልማትና ለውጥ እንዳይመጣ የሚያግድ ምንም አይነት ምክንያት አይኖርም" ያሉት አቶ ጸጋዬ "ሰላማችንን መጠበቅ ያስፈልጋል" ሲሉ በአጽእኖት ተናግረዋል።

"ለዘላቂ ልማትና ዕድገት ተቻችሎና ተከባብሮ መኖር ያስፈልጋል" ያሉት አቶ ፀጋዬ ማንኛውም የልማትና መልካም አስተዳደር እንዲሁም የመዋቅር ጥያቄዎች ቢኖሩ እንኳ በሰላማዊ መንገድ በውይይት ብቻ መፍታት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ለልማት አውታሮች መስፋፋት ሰላም ያለውን ሚና በመረዳት ሁሉም ለሰላም ዘብ መቆም እንዳለበት አሳስበዋል ።

ለምረቃ የበቃው የሸኮ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ የተሟላ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የክልሉ ክህሎትና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ እንዳሻው በበኩላቸው እንዳሉት የቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት በመካከለኛና ዝቅተኛ ደረጃ የሰለጠኑ ብቁና ለሥራ ፈጠራ ዝግጁ የሆኑ ወጣቶችን ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና አላቸው።

ክልሉ የተቋማቱን ተልእኮ ከግብ ለማድረስ  እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው ሌሎች ዘጠኝ የኮንስትራክሽን እና ኢንዱስትሪያል ኮሌጆች በተለያዩ ወረዳዎች እየተገነቡ መሆኑን ተናግረዋል።

ዛሬ ተመርቆ ለአገልግሎት የተዘጋጀው የሸኮ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ በቴክኖሎጂና ተያያዥነት ባላቸው መስኮች አገልግሎት በመስጠት ለማኅበረሰብ ለውጥ መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ከ39 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የሸኮ ኮንስትራክሽን እና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ በሦስት የትምህርት መስኮች 120 ተማሪዎችን በመቀበል ሥራ እንደሚጀምር የገለጹት ደግሞ የቤንች ሸኮ ዞን ክህሎትና ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ስንቁ ነጋሽ ናቸው።

በኮንስትራክሽን፣ በማኑፋክቸሪንግ እና በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ  እንዲያሰለጥን እውቅና የተሰጠው ኮሌጁ በቀጣይ በአውቶሞቲቭ፣ ኤሌክትሪክሲቲ እና በቅየሳ ስልጠና እንዲሰጥ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል።

ህዳር 01 ቀን 2010 ዓም የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት ኮሌጁ በተለያዩ ምክንያቶች የግንባታ ሥራው ተጓቶ ቆይቶ በዛሬው እለት ለምረቃ መብቃቱን  አቶ ስንቁ አስታውቀዋል።

በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልን ጨምሮ የዞንና ወረዳ አመራሮችና የአከባቢው ማህበረሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም