የሆስፒታሉ የክፍል ጥበትና የአልጋ እጥረት ችግር መቃለሉ ተገለጸ

116
ባህርዳር መስከረም4/2011 በባህርዳር ፈለገ ህይወት ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል ቀደም ሲል በክፍል ጥበትና በአልጋ እጥረት ምክንያት ያጋጥማቸው የነበረው ችግር መቃለሉን ወላድ እናቶች ተናገሩ። ችግሩ የተቃለለውም የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በሆስፒታሉ ግቢ ለተማሪዎች ማደሪያ ያስገነባውን ባለአምስት ፎቅ ህንፃ ለሆስፒታሉ ድጋፍ በማድረጉ ነው። በባህርዳር ከተማ የሽምብጥ ክፍለ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ማማሩ ማንአየ ለኢዜአ እንዳሉት  ከዚህ ቀደም የመጀመሪያ ልጃቸውን በሆስፒታሉ ሲውልዱ በአልጋ እጥረት ምክንያት የተስተናገዱት መሬት ላይ ነበር። ከጥበቱ የተነሳም ሌሎች ወላድ እናቶችን ለማስተናገድ ሲባል ሳይረጋጉ ሆስፒታሉን ለቀው እንዲወጡ ይደረግ እንደነበርም አስታውሰዋል። " አሁን ሁለተኛ ልጃቸውን ለመውለድ ሲመጡ ተጨማሪ ህንፃ ተገንብቶ በማግኘቴ ሳልሳቀቅ ንፅህናው በተጠበቀ ክፍልና አልጋ መተኛት በመቻሌ የራሴንም ሆነ የልጄን ጤና እንዲጠብቅ ምቹ ሆኖ አግኝቼዋለሁ" ብለዋል። ሌላኛዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ፀሐይ ጫኔ በበኩላቸው በሆስፒታሉ የወላዶች የመኝታ ክፍል ጥበት አሁን ተቃሎ በማግኘታቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል። የነበረው የክፍል ጥበት ችግር በመቃለሉም ምቾት ባለው  የመኝታ አልጋ ከነልጃቸው በመተኛት እንክብካቤ እያገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሞላልኝ ታረቀኝ እንደገለጹት በሆስፒታሉ ከሚነሱት ችግሮች መካከል የአገልግሎት መስጫ ክፍሎች ጥበት ዋነኛው ነበር፡፡ ከክፍል ጥበትና ከአልጋ እጥረት ጋር ተያይዞም ከሆስፒታሉ ወደሌላ ጤና ተቋም እናቶች እንዲሄዱ ይደረግ እንደነበር ጠቁመው "የሚወልዱትም ከአልጋ እጥረት ጋር ተያይዞ ኮሪደር መሬት ላይ እንዲተኙ ይደረግ ነበር" ብለዋል። ይህም የወላድ እናቶችን ክብር ዝቅ ከማድረጉም በላይ የጤና ሙያዊ ስነ ምግባር ጉድለት ሆኖ እንደቆየ ተናግረዋል። ችግሩን ለመፍታት ሆስፒታሉ ከክልሉ ጤና ቢሮ፣ ከቦርድ አመራሮችና ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመነጋገር ዩኒቨርስቲው  ለሌላ አገልግሎት ያስገነባው ህንፃ ለወላዶች አገልግሎት እንዲውል በመደረጉ ችግሩ መቃለሉን ገልጸዋል። የተገነባው ህንፃ ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ ባይሆንም እናቶች መሬት ከሚተኙ ባለቁ ክፍሎች 135 አልጋዎችን ከዩኒቨርሲቲው በማስገባት ወላድ እናቶች እንዲስተናገዱበት እየተደረገ ነው። የተገነባው ባለአምስት ፎቅ ህንፃ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ሲበቃም 360 አልጋዎችን በመያዝ ከእናቶች በተጨማሪ ሆስፒታሉ ያሉበትን ሌሎች የክፍል ጥበት ችግር እንደሚያቃልል አቶ ሞላልኝ አስረድተዋል። የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ለተማሪዎች ማደሪያ ያስገነባውን ባለአምስት ፎቅ ህንፃ ወላድ እናቶች እንዲገለገሉበት ለሆስፒታሉ የሰጠው በጊዜያዊነት እንደሆነም ተመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም