በክልሉ በዘንድሮ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ67 ሺህ በላይ ወጣቶች ይሳተፋሉ – ቢሮው

199

አሶሳ፤ ሐምሌ 8 / 2014 ( ኢዜአ)፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በዘንድሮው ክረምት በሚከናወነው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ67 ሺህ በላይ ወጣቶች እንደሚሳተፉ የክልሉ ሴቶች ህጻናት እና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ሃላፊ ወይዘሮ ሃጅራ ኢብራሂም  ለኢዜአ እንደገለጹት በ12 ዘርፎች ያተከረ  ዓመታዊ የክልሉ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በቅርቡ ይጀመራል፡፡

በበጎ ፈቃድ ስራው 67 ሺህ 881 ወጣቶች እንደሚሳተፉ አመልክተው፤ “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሀሳብ  በሚተገበረው አገልግሎት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ቀዳሚው መሆኑን ተናግረዋል።

ህገ-ወጥ የሰዎችን ዝውውር መከላከል፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት መጠገን፣ ሰላም ና ደህንነት ማጠናከር፣ የከተማ ጽዳትና ውበት፣ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጎቶችን ጨምሮ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን መከላከል የወጣቶች ስብዕና ግንባታ እና ሌሎችም የመርሐ ግብሩ አካል መሆናቸውን አመልክተዋል።፡

በመርሐ ግብሩ የሚሳተፉ ወጣቶች እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያሉ ተማሪዎች፣ የወጣቶችና ሴቶች ፌዴሬሽኖች አደረጃጀት አባላት፣ የተለያዩ ማህበራት አባላት በመንግስታዊና  መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የሚገኙ እና ሌሎችም  መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የእቅዱን አፈጻጸም ስኬታማ ለማድረግ  ከሌሎች መንግስታዊ ተቋማት ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።  

የበጎ ፈቃድ ስራው ስድስት ሚሊዮን ብር የሚገመት ወጪ  እንደሚያድን ጠቅሰው፤ ”በአገልግሎቱ ከ278 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ይደረጋል” ብለዋል።

ከአሶሳ ከተማ ወጣቶች መካከል መንግስቱ ቀኖ እንደገለጸው ወጣቱ በበጎ ፈቃድ ስራ በመሳተፍ አካባቢውን ለማልማት የመንግስትንም ሆነ የሌላ አካል ቅስቀሳ ሊጠብቅ አይገባም።

”በተለይም አቅመ ደካማ ሰዎችን መርዳት ያስደስተኛል” ያለው ወጣቱ፤ ይህን ፍላጎቱን በመጪው የክረምት በጎ ፈቃድ ለማከናወን ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ከስድስት ዓመታት በላይ በበጎ ፈቃድ ስራ መሳተፉን  የተናገረው ደግሞ መምህር እርቅነው መንግስቱ ነው።

በጎ ፈቃድ ከሃይማኖት፣ ከፖለቲካ ና ከሌሎችም ዓላማዎች ነጻ በመሆን የሚሰጥ አገልግሎት መሆኑን አመልክቶ፤በፕሮግራሙ መሳተፍ የህሊና እርካታ እንደሚሰጥ አመልክቷል።