የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር በ10 ዓመት ውስጥ የትራፊክ አደጋን በ50 በመቶ ለመቀነስ መታቀዱን ገለጸ

233

ሐምሌ 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) የትራፊክ አደጋን በ10 ዓመት ውስጥ በ50 በመቶ ለመቀነስ መታሰቡን የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ በአገር አቀፍ ደረጃ በመንገድ ትራፊክ አደጋ የሚመጣ ሞትና የአካል ጉዳትን መቀነስ ያስችለኛል ያለውን የ10 አመት የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂ ዛሬ ይፋ አድርጓል።

ስትራቴጂውን ይፋ የማድረግ መርሃ ግብር ላይ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ፣ የተጠሪ ተቋማት አመራሮች፣ የከተማ ከንቲባዎች፣ የፌደራልና የክልል ባለድርሻ አካላት፣ የዓለም አቀፍ ድርጅት ኃላፊዎችና የአጋር ድርጅቶች ተወካዮች ተገኝተዋል።

የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂው እ.አ.አ በ2030 የትራፊክ አደጋን በ50 በመቶ የመቀነስ ግብ መያዙ ተገልጿል።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት እንዳሉት፤ ስትራቴጅው በአገር አቀፍ ደረጃ በመንገድ ትራፊክ አደጋ የሚመጣ ሞትና የአካል ጉዳትን ለመቀነስ ያለመ ነው።

ስትራቴጂው ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችንና መስፈርተኞችን ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ተናቦ እንዲዘጋጅ መደረጉን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም