የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማሳደግ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

154

ሐምሌ 08 ቀን 2014 (ኢዜአ)  የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስርዓተ-ጾታ እኩልነትና ሴቶችን ማብቃት ተቋም (ዩ.ኤን.ውመን) ጋር የሴቶችን ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማሳደግ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ።

ተቋማቱ የሴቶችን እኩልነት በማረጋገጥ ሴቶችን ለማብቃት እና ለመደገፍ የሚያስችላቸውን ስምምነት ነው የተፈራረሙት፡፡

የስምምነት ሰነዱን የተፈራረሙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስርዓተ-ጾታ እኩልነትና ሴቶችን ማብቃት ተቋም (ዩ.ኤን.ውመን) ምክትል ተወካይና ጊዜያዊ ዋና ተጠሪ ሚስተር ሻድራክ ዱሳቤ ናቸው።

የፊርማ ስነስርአቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስርዓተ-ጾታ እኩልነትና ሴቶችን ማብቃት ተቋም (ዩ.ኤን.ውመን) የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ቀጣና ቢሮ ዳይሬክተር ዶክተር ማክሲም ሀዊናቶ በተገኙበት ነው የተከናወነው፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ስምምነቱ  በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ከፍ የሚያደርግ ነው፡፡

ግጭት በሚኖርበት ወቅት ሴቶች የመጀመሪያ ተጎጂ መሆናቸውን ጠቅሰው ለአራት ዓመታት የሚቆየው ይህ ስምምነት ሴቶች ሰላምና ደህንነታቸው ተጠብቆ በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስርዓተ-ጾታ እኩልነትና ሴቶችን ማብቃት ተቋም (የዩኤን ውመን) የምስራቅ  ደቡብ አፍሪካ ቀጠና ቢሮ ዳይሬክተር  ዶክተር ማክሲም ሀዊናቶ በበኩላቸው፤ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጾታዊ ትንኮሳ ለመከላከልና የሴቶችን የውሳኔ ሰጭነት ሚና ለማሳደግና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ስምምነቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ስምምነቱ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና በዩኤን ውመን መካከል ከአስር አመት በላይ የዘለቀውን ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያጠናክር ተገልጿል፡፡